ህወሃት በክልሉም ሆነ ከክልሉ ውጪ ለሚገኘው ትግራዋይ የፈታው ችግር የለም...የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ - ኢዜአ አማርኛ
ህወሃት በክልሉም ሆነ ከክልሉ ውጪ ለሚገኘው ትግራዋይ የፈታው ችግር የለም...የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ
ድሬዳዋ መስከረም 28/2013 (ኢዜአ) የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በድሬዳዋ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ገለጹ።
ህወሃት በክልሉም ሆነ ከክልሉ ውጪ ለሚገኘው ትግራዋይ ያመጣውና የፈታው ችግር እንደሌለ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ አስታውቋል።
ዛሬ በድሬዳዋ ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ከክልላቸው የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ የተሳተፉት አቶ የማነ ወልዳይ እንደተናገሩት በሀገር ውስጥ የተረጋጋ ሰላምን ማስጠበቅ የሁሉም ኃላፊነት ነው።
የፖለቲካ ፓርቲዎችም በመሃላቸው ያለውን ችግር በውይይት በመፍታት ለሀገር ሰላምና ዕድገት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚባ ተናግረዋል።
"የብልጽግና ፓርቲ በትግራይ ክልል ውስጥ ያለውን አደረጃጀት በማጠናከርና ከህብረተሰቡ ጋር በመቀራረብ የህዝቡን ችግር ለመፍታት በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል" ያሉት ደግሞ አቶ ደስታ ፀጋዬ ናቸው፡፡
በድሬዳዋ ከሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በፍቅርና በአንድነት ለአካባቢው ሰላም፣ ልማትና ሀገሪቱ ወደ ተሻለ የዕድገት ጎዳና እንድትጓዝ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ወይዘሮ ትግዕስት ወልደ መስቀል በበኩላቸው “የፌደራል መንግስት ለትግራይ ክልል የሚሰጠው በጀት በትክክል ለጤና፣ለትምህርት ፣ለማበራዊና ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲውል መንግስት ክትትልና ቁጥጥሩን ማጠናከር አለበት” ብለዋል።
“በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን እኛ ዜጎቿ በፍቅርና በአንድነት ተባብረን ያለችንን አንድ ሀገር ለማሳደግ እንሰራለን” ብለዋል።
አቶ ኤፍሬም ግርማይ የተባሉ የመድረኩ ተሳታፊ በበኩላቸው የትግራይ ህዝብን በስፋት ስለ ብልጽግና ፓርቲ በማስተማር ህዝቡን ከህውሃት መለየት እንደሚገባ ገልፀዋል።
መንግስት በሌብነትና በወንጀል ላይ የተገኙ አጥፊዎችን ለህግ በማቅረብ የህግ የበላይነት ማረጋገጥ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ወጣት አሸናፊ ታደሰ በበኩሉ መንግስት ህዝብን በህዝብ ላይ ለማነሳሳት ቀንና ማታ የሚሰብኩና የሚያውጁ መገናኛ ብዙሃንን፣ አክቲቪስቶችንና ፖለቲከኞችን አሁንም መንጥሮ ለህግ ማቅረብ እንዳለበት ጠይቋል።
ወጣቱ የህዝብ አብሮነት የሚሸረሽሩና የሚያናጉ አካላትን ለመዋጋት፤ የሀገሪቱን ሰላም ፣አንድነትና ዕድገት ለማረጋገጥ ከጓደኞቹ ጋር ሌት ተቀን ለመስራት መዘጋጀቱን ተናግሯል።
ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ብርሃኑ ፍፁም የሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው ገልፀው በገመድ ሣይሆን በደም የተሳሰረው የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን በመጠበቅ የሀገሪቱን ዕድገት ማስቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
የተዘጉ መንገዶች እንዲከፈቱ በማድረግና ሁሉንም ችግሮች በሰላማዊ መንገድ በመፍታት የሀገሪቱን መፃኢ ዘመን በተደላደለ የሰላም መሰረት ላይ ማዋቀር እንደሚገባ ተናግረዋል።
መድረኩን የመሩት የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶክተር አብርሃም በላይ ባስተላለፉት መልዕክት ህውሃት በክልሉም ሆነ ከክልሉ ውጪ ለሚገኘው ትግራዋይ ያመጣውና የፈታው ችግር እንደሌለ በአጽንኦት አስረድተዋል።
“የብልጽግና ፓርቲ ይህን ችግር ለመፍታት የሀገሪቱ ብሔር ብሔረቦች በአንድነት፣ በነፃነት ፣በእኩልት የሚገነቧትና የሚጠቀሙባት ጠንካራ የበለፀገች ሀገር ለመገንባት እየሰራ ይገኛል” ብለዋል።
በመሆኑም በየትኛውም የሀገሪቱ ክልል የሚገኝ ትግራዋይ መብቱና እኩልነት ተጠብቆለት እንዲንቀሳቀስ ብልጽግና ፓርቲ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ዶክተር አብራሃም አስረድተዋል።
ብልጽግና ከሰላምና ከሃሳብ ልዕልና በስተቀር ለአፍታም ቢሆን ስለጦርነት የሚያስብበት ጊዜ የለውም ያሉት ዶክተር አብርሃም ከትግራይ ህዝብ ላይ የሚነካና የሚቆረጥ አንድም በጀት እንደሌለም ገልጸዋል።
በመሆኑም በክልልም ሆነ ከክልሉ ውጪ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች የብልጽግና ፓርቲ የጀመረው የሰላም፣ የልማትና የብልጽግና ጉዞ በስኬት እንዲጠናቀቁ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡