አለርት ሆስፒታል ከ500 በላይ ለሚሆኑ ሕሙማን ነጻ የዓይን ምርመራና የሕክምና አገልግሎት ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
አለርት ሆስፒታል ከ500 በላይ ለሚሆኑ ሕሙማን ነጻ የዓይን ምርመራና የሕክምና አገልግሎት ሰጠ
መስከረም 28/2013 (ኢዜአ) አለርት ሆስፒታል የዓለም ዕይታ ቀንን ምክንያት በማድረግ ከ500 በላይ ለሚሆኑ ሕሙማን ነጻ የዓይን ምርመራና የሕክምና አገልግሎት ሰጠ።
በአውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ2000 ጀምሮ በየዓመቱ በጥቅምት ወር መጀመሪያ ሳምንት ላይ የሚከበረው የዓለም የዕይታ ቀን "ተስፋችን በዕይታችን " በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በአለርት ሆስፒታል በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
የሆስፒታሉ የዓይን ሕክምና ክፍል ኃላፊ ዶክተር ሰለሞን ቡሳ እንዳሉት ቀኑን በማስመልክት ከ500 በላይ ለሚሆኑ ሕሙማን በሆስፒታሉ ነጻ የዓይን ምርመራ፣ የሕክምና እና የመነጽር አገልግሎት አግኝተዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ ከ70 እስከ 80 በመቶ የዓይነ ስውርነት መንስኤዎች ቀድሞ መከላከል ይቻላል።
በመሆኑም ህብረተሰቡ አመጋገቡን በማስተካከል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማዘውተር እንዲሁም ከ6 እስከ 8 ሰዓት የሚደርስ በቂ እንቅልፍ በመውሰድ የዓይኑን ጤናን መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በተለይ የስኳር ሕመም ያለባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ የዓይን ምርመራን ማድረግ እንዳለባቸውም ነው የጠቆሙት።
ሕብረተሰቡ አትክልቶችን እንዲሁም የቫይታሚን "ሲ" እና "ኤ" ይዘት ያላቸውን ምግቦችን በመመገብ የዓይኖቹን ጤና እንዲጠብቅም መክረዋል።
የዓይን ሕክምና አገልግሎት ላይ የሚሰራው ክርስቲያን ብላይንድ ሚሽን ኢትዮጵያ (ሲ.ቢ.ኤም-ኢትዮጵያ) የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ፍራንሲስኮ ጂሉቲቲ በበኩላቸው ድርጅታቸው የዓይን ህክምና አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልፀዋል።
በአውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2020 እስከ 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ በአዲስ አበባ፣ በአማራ፣ በትግራይ እና በደቡብ ክልሎች በዓይን ጤና ላይ አተኩረው የሚተገበሩ 39 ፕሮጀክቶች መቀረጻቸውንና ለፕሮጀክቶቹም በድርጅቱ በኩል 4 ሚሊዮን ዩሮ መመደቡን አስረድተዋል።
ፕሮጀክቶችን በመጠቀም በመላ አገሪቱ ለሕሙማን የሚሰጠው የዓይን ሕክምና አገልግሎት ጥራት እንዲሻሻል በሚደረገው ጥረት ድርጅቱ የበኩሉን እንደሚወጣም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
በበዓሉ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስቴር ተወካይ አቶ አዲሱ ወርቁ ሚኒስቴሩ በዘርፉ ያለውን የሰው ሀብት እጥረት ለመቅረፍ ስልጠና እየሰጠ መሆኑንና የዓይን ህክምናን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በተለያዩ የሕክምና ተቋማት አገልግሎቱ እንዲሰጥ መደረጉን አመልክተዋል።
ለእዚህም ለዓይን ሕክምና አገልግሎት ትኩረት እንዲሰጠው በየሕክምና ተቋማቱ ራሱን የቻለ ኬዝ ቲም እንዲቋቃም መደረጉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
የበዓሉ መከበር ህብረተሰቡ ስለዓይን ጤና ያለውን ግንዛቤ ለማዳበር የሚያስችል መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ ለዓይነስውርነት ከሚያጋልጡ መንስኤዎች ውስጥ የሞራ ግርዶሽ 49 ነጥብ 9 በመቶ፣ ትራኮማ 11 ነጥብ 5 በመቶ፣ ግላኮማ 5 ነጥብ 2 በመቶ እንደሚይዙ መረጃዎች ያሳያሉ።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 1 ሚሊዮን 760 ሺህ ዓይነ ስውራን እንዳሉ የተገለጸ ሲሆን የዓይነ ስውርነት የስርጭት መጠን ደግሞ 1 ነጥብ 6 በመቶ ነው ተብሏል።