ቀጥታ፡

በሀገሪቱ የግል አምራች ዘርፍ ከ2 ሚሊዮን ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል ለማመቻቸት እየተሰራ ነው

ሀዋሳ መስከረም 28/2013 (ኢዜአ) በሀገሪቱ የግል አምራች ዘርፍን በማጠናከር ከ2 ሚሊዮን ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል ለማመቻቸት እየሰራ መሆኑን የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለሥልጣን አስታወቀ።  

ባለስልጣኑ በ2012 በጀት ዓመት  አፈጻጸምና በተያዘው የስራ ዘመን እቅድ ዙሪያ ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ  ተጀምሯል።

በዚህ  ወቅት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ  እንዳሉት የስራ እድሉ የሚመቻቸው እሰከ 2017 ዓ.ም ድረስ ነው።

ዘርፉ በርካታ ዘጎችን በቀጥታና ተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል ቢሆንም ካሁን በፊት የነበረው አሳታፊነት የጎደለው አሠራር ውጤታማ እንዳይሆን ማድረጉን ተናግረዋል።

በለውጥ ሂደት በሀገሪቱ የተጀመረው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም በዋናነት የግሉን አምራች ዘርፍ ውጤታማና ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዲሆን የሚያበረታታ ነው ብለዋል።

መንግስትም ዘርፉ በሀገሪቱ የልማት ግብ ላይ መጫወት የሚገባውን ሚና እንዲወጣ ለማድረግ ልዩ ትኩረት መስጠቱን አስታውቀዋል።

እስካሁን በሀገሪቱ  የተቋቋሙ 20 ሺህ የማይበለጡ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ለ500 ሺህ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል እንዳመቻቹ ጠቁመው ይህ ከሀገሪቱ የህዝብ ቁጥር አንጻር አነስተኛና ዘርፉ በቂ ሚና እየተጫወተ አለመሆኑን ያሳያል ብለዋል።

ባለስልጣኑ  በመንግስት ደረጃ የተሰጠውን ትኩረት መነሻ በማድረግ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅዶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ የኃይል፣ፋናንስና ማምረቻ ቦታ አቅርቦት ላይ  አሠራሮች ለማዘመንና የገበያ ትስስር ለማጠናከር መታቀዱንም ጠቁመዋል።

በተለይ የውጭ ምርቶችን በማስቀረትና ሃገር በቀል ምርቶች የሚኮራ ማህበረሰብ ለመፍጠር አምራች ዘርፉ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

ትልልቅ ኢንዱስትሪዎችን ከአነስተኛና መካከለኛዎች ጋር ተቀናጅተው የሚሠሩበትና የመንግስት የግዥ ሥርዓት ሃገር በቀል ምርቶች ላይ ትኩረት እንዲሰጥ መግባባት ላይ መደረሱ ጠቁመው ይህም  ለዘርፉ ማደግ ወሳኝ እንደሆነ አብራርተዋል።

የሲዳማ ክልል ሥራ ዕድል ፈጠራ አንተርፕራይዞችና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሠላሙ ቡላዶ  በበኩላቸው የአምራች ዘርፉን ተሳትፎ በማሳደግ የዜጎች ተጠቃሚነት ማሳደግ እንዲቻል  ኢንዱሰትሪዎችንና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የቅንጅት ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።

በዚህም በክልሉ በሚገኙ ሶስት ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጨምሮ ሌሎችንም በማበረታታ በተያዘው ዓመት ከ103 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች  የሥራ ዕድል ለመፍጠር  መታቀዱን ተናግረዋል።

ሌላው የመድረኩ ተሳታፊና የጋምቤላ ክልል ኢንዱስትሪ ዘርፍ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡጉሎ ጁሊ በክልሉ  በአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ የግሉን ዘርፍ ለማበረታታ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በተለይ በተያዘው የበጀት ዓመት ዘርፉን በመደገፍ ለ3 ሺህ 770 ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን ገልጸዋል።

ባለፉት ጊዜያት ዘርፉ በተፈለገው መልኩ ትኩረት እንዳላገኘ የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሉ ጉርሙ ናቸው።

አሁን ላይ መንግስት ለአነስተኛ አምራች ዘርፎች የሰጠው ትኩረት የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸው ይህንን እድል በመጠቀም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚፈለገውን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በመድረኩ ከክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ፣የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን፣የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች እየተሳተፉ ነው።

ተሳታፊዎች  ይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክን እንደሚገበኙም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም