ዩኒቨርሲቲው የተማሪ ቅበላ አቅሙን በሦስት እጥፍ ለማሳደግ አቅዷል - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው የተማሪ ቅበላ አቅሙን በሦስት እጥፍ ለማሳደግ አቅዷል
አክሱም መስከረም 28/2013 (ኢዜአ) አክሱም ዩኒቨርሲቲ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት አጠቃላይ የተማሪ ቅበላ አቅሙን በሦስት እጥፍ ለማሳደግ ማቀዱን አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው በአሥር ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዱ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይቷል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ገብረእየሱስ ብርሃነ በወቅቱ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የአሥር ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አውጥቶ ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ ነው።
በስትራቴጂክ ዕቅዱ በመጭዎቹ አሥር ዓመታት አሁን የደረሰበትን 25 ሺህ አጠቃላይ የተማሪ ቅበላ አቅም በሦስት እጥፍ ለማሳደግ አቅጣጫ መያዙን አመላክተዋል።
በዓመታቱ ውስጥ 80 አዳዲስ የትምህርት ዘርፎች ለመክፈት መታቀዱን ጠቁመው ከሚከፈቱት የትምህርት ዘርፎች ውስጥ 78 በመቶው በድኅረ ምረቃ መርሀ ግብር የሚሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የሰለጠነ የሰው ኃይል በብዛት ከማፍራት ጎን ለጎን የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥና የቴክኖሎጂ ሽግግርን እውን ማድረግ የስትራቴጂክ ዕቅዱ ዋና ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ስትራቴጂክ ዕቅዱን እውን በማድረግ የተጣለበትን ሀገራዊ ተልዕኮ በአግባቡ ለመወጣት የተቋማዊ ለውጥ ማሻሻዎችን በማዘጋጀት ሥራ ላይ ለማዋል እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የሠራተኞች አቅም ማጎልበትም የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች አንድ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲይዙና በተነሳሽነት እንዲሠሩ ለማድረግ ቀጣይነት ያለው ሥራ እንደሚሠራም ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።
የዩኒቨርሲቲው ስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጅ ኮሚቴ አባልና የምርምርና ኅትመት ዳይሬክተር ዶክተር መዋዕል ብርሃነ በበኩላቸው ዕቅዱ ሲዘጋጅ ብቁ ምሩቃን ማፍራት፣ ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን ማካሄድና የማኅበረሰብ አገልግሎትን ማሰፋፋት ዓላማ በማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።
ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የዩኒቨርሲቲዎች ትብብርና ግንኙነት በማጠናከርም ሌላው የዕቅድ ዝግጅቱ ዓላማ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዕቅዱን ለማሳካት የአሠራር፣ የመሠረተ ልማትና የሰው ኃይል ልማት የመሳሰሉ አስፈላጊ ግብአቶች ተለይተው አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን አመላክተዋል።
"የተቀመጡ ስትራቴጂክ ዓላማዎችና ፕሮግራሞች እውን ለማድረግ በየዓመቱ በሚሠሩ ሥራዎች ላይ በማትኮር መከወን ይገባል" ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር አብርሃ ገብሩ ናቸው።
መምህራንና የአስተዳደር ዘርፉ በቅንጅት የሚሠሩበት ሁኔታን ማመቻቸት እንደሚገባም ዶከተር አብርሃ አስታውቀዋል።