ቀጥታ፡

አገራዊ መግባባትን የሚፈጥር የምክክር ኢኒሼቲቭ ተመሠረተ

አዲስ አበባ መስከረም 28/2013 (ኢዜአ) ሁሉን አቀፍ አገራዊ መግባባትን መፍጠር ዓላማው ያደረገ የምክክር እኒሼቲቭ ተመሠረተ።

ኢኒሼቱቩ የተመሠረተው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ ዶስቲኒ ኢትዮጵያና የሀሳብ ማዕድ በተባሉ ተቋማት ነው።

ኢኒሼቲቩን በጋራ ያቋቋሙት አካላት ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ሰብሳቢ አቶ ሙሣ አደም በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ኢኒሼቲቩ አገራዊ መግባባት የሚፈጥሩ ሀሳቦች የሚነሱበት ነው።

በተጨማም እርስ በእርስ የሚያጋጩ የሀሳብ  ልዩነቶችን ከማቀራረብ  ባሻገር  በተሳታፊዎች መካከል መልካም ግንኙነትና የአንድነት መንፈስ የሚያጎለብቱ ሐሳቦች እንደሚቀርቡበት ገልጸዋል።

በኢኒሼቴቩ  የሚካሄደው ውይይትም የተሳታፊዎችን ደህንነትና ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት ባስከበረ መልኩ እንደሚከናወንም አስረድተዋል።

ውይይቱ በምዕራፎች ተከፋፍሎ ቀጣይነት ባለው መንገድ እንደሚከናወን አመልክተዋል።

ዋና ሰብሳቢው እንዳሉትለዚህም አገራዊና ባህላዊ እሴቶችን ያማከለና ሙያዊ መንገድ ይከተላል ብለዋል።

የተለያዩ ሀሳቦችን በአንድ መድረክ ላይ አገናኝቶ ወደ አንድ አቅጣጫ ማምጣት የኢኒሼቲቩ ዋነኛ ዓላማ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የአገሪቱን አንድነትና የሕዝቦችን መግባባት የሚያመጡ ጥያቄዎችና ሀሳቦች እንደሚንሸራሸሩበት አቶ ሙሣ  ገልጸዋል።

በአገር ደረጃ የሚደረገው ኢኒሼቲቭ ከሰላም ሚኒስቴር ዕውቅና ማግኘቱንም ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ አስተዳደራዊ፣ ፖለቲካዊና የደህንነት ድጋፍ ለመስጠትና የሂደቱ አካል ለመሆን የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙን አቶ ሙሣ ገልጸዋል።

የዴስቲኒ ኢትዮጵያ አስተባባሪ አቶ ንጉሡ አክሊሉ በበኩላቸው ኢኒሼቲቩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማኅበራትን፣ ወጣቶችን፣ ሴቶችን፣ አርሶ አደሮችን፣ አርብቶ አደሩን ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች እንደሚወከሉበት አብራርተዋል።

የሀሳብ ማዕድ አስተባባሪ ዶክተር አደራ አብደላ እንዳሉትም የመሥራቾቹ ተቋማት ሚና መድረኩን ማመቻቸትና ድጋፍ መስጠት ነው ብለዋል።

የውይይት አጀንዳ ከመቀረጽ ጀምሮ መግባባት ላይ መድረስና የአገሪቱን አንድነት ለማስቀጠል ሚና መጫወት የተወያዮች ድርሻ ነውም ሲሉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

ኢኒሼቴቩ  በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ  መድረኮችን ማዘጋጀት እንደሚጀምርም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም