የትግራይ ህዝብ ከለውጡ እንዲጠቀም እየሰራ መሆኑን የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ህዝብ ከለውጡ እንዲጠቀም እየሰራ መሆኑን የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ
ደሴ መስከረም 28/2013( ኢዜአ ) የትግራይ ህዝብ ከሀገራዊ ለውጡ ተጠቃሚ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን የትግራይ ክልል ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ፡፡
ፓርቲው ከደሴ፤ ኮምቦልቻና ሐይቅ ከተማ የትግራይ ተወላጆች ጋር በወቅታዊ ጉዳች ዙሪያ ዛሬ በደሴ ከተማ ተወያይቷል፡፡
በዚህ ወቅት የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነብዩ ስሁል ሚካኤል እንደገለጹት ለኢትዮጵያ ዳር ድንበር መከበርና አንድነት የትግራይ ህዝብ መስዋትነት ከፍሏል፡፡
አሁን ለተገኘው ሀገራዊ ለውጥም ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቹ ጋር የራሱን ኃላፊነት ቢወጣም በግልና ቡድን ጥቅመኞች ምክንያት ከለውጡ ተጠቃሚ መሆን አልቻለም ብለዋል፡፡
ህዝቡ የለውጡ ተጠቃሚ እንዲሆንም ብልጽግና ፓርቲ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠረው የጸጥታ ችግር የህዝቡ ሳይሆን የፖለቲከኞች ሴራ ነው ያሉት ኃላፊው የትግራይ ህዝብ በየትኛውም አካባቢ ያለ ስጋት ሰርቶ እንዲኖር ፓርቲው ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አስታውቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ከሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ጋር በመወያየትና ግንዛቤ በመፍጠር ያለውን ሀገራዊ ሁኔታ በማስረዳት አንድነትንና ሰላሙን እንዲጠብቅ እንሰራለንም ብለዋል፡፡
የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶክተር ሙሉ ነጋ በበኩላቸው ከትግራይ ምሁራንና ህዝብ ጋር በመወያየት የለውጡ ተጠቃሚ ለመሆን እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
በህወሓት ያረጀ ግትር ሀሳብና የውሸት ትርክት ህዝቡ መደናገር የለበትም ያሉት ዶክተር ሙሉ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለውጡ እንዲቀጥልና ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በሁሉም ህዝብ ትግል ከመጣው ለውጥ የትግራይ ህዝብ መጠቀም አለበት፤ በየትኛውም አካባቢ የሚኖር የትግራይ ተወላጅ እውነቱን ተረድተው ለሀገራዊ አንድነቱ የራሱን አሻራ ማስቀመጥ አለበት ብለዋል፡፡
የግል ጥቅመኛ ግለሰቦችና ቡድኖች ህብረተሰቡን እያወናበዱ መቀጠልና በዚህ በሰለጠነ ዘመን ይህን መፍቀድ እንደማይገባ አመልክተዋል፡፡
የትግራይ ህዝብ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ በኢኮኖሚ፤ ፖለቲካና ማህበራዊ ጉዳዮች እኩል እንዲሳተፍና እንዲጠቀም ፓርቲው በትኩረት እንደሚሰራም አስታውቀዋል፡፡
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አንዳንዳቹ በሰጡት አስተያየት ለውጡ እንዲመጣ የትግራይ ህዝብ ትግል ቢያደርግም ከዚህ ተጠቃሚ አለመሆኑ እንደሚያሳዝናቸው ተናግረዋል።
በህዝብ ደም የራሱን ጥቅም እያካበተ ያለውን ህውሓት ከዚህ በኋላ መታገስ እንደማይገባ ጠቁመው አንድነታቸውን አጠናክረው ለሰላም የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡
በአካባቢያቸው ላሉ የትግራይ ተወላጆችም ግንዛቤ በመፍጠር ህዘቡን ከኢትዮጵያ ህዝብ ለመነጠል የሚሰሩ ፖለቲከኞችን እንደሚታገሉም አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ እንዳትደፈር በርካታ የትግራይ ወጣቶች መስዋዕትነት መክፈላቸውንም አስረድተዋል።
ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሆነው መስዋዕት ከሆኖላት ሀገራቸው ለመነጠል የሚሰራውን ሴራ እንደሚቃወሙ አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸው ፤ ለሀገር አንድንትና ሰላም የበኩላቸውን እንደሚወጡም አስታውቀዋል፡፡
ህወሕት ሀገርን ለማፍረስና ለማበጣበጥ የሚሰራ ፓርቲ እንጂ የትግራይን ህዝብ ተጠቅሞ እንደማያውቅ ጠቁመው እንዲያውም ህዝቡ ጥቅም ባላየበት ተሳቆ እንዲኖር መደረጉን አስረድተዋል፡፡
ከብልጽግና ፓርቲ ጋር በቅንጅት በመስራት የብልጽግና ተቋዳሽ ለመሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ አመራሮችና ደጋፊዎች ተሳትፈዋል፡፡