ቀጥታ፡

የህወሃት አመራሮች ረስትውት በኖሩት የትግራይ ህዝብ ለመጠቀም የሚያደርጉት ጥረት ተቀባይነት የለውም…በባህርዳር የትግራይ ተወላጆች

ባህር ዳር መስከረም 28/2013(ኢዜአ) የህወሃት አመራሮች ረስተውት በኖሩት የትግራይ ህዝብ ለመጠቀም የሚያደርጉት ጥረት ተቀባይነት እንደሌለው በባህርዳር ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ገለጹ። 

የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ዛሬ በባህርዳር ከተማ ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ጋር ውይይት አካሒዷል።

በባህር ዳር ከተማ ለ40 አመት ገደማ እንደኖሩ የገለጹት የውይይቱ ተሳታፊ መመህር ሃብቶም ሃዱሽ እንደገለጹት በከተማው የሚኖር ትግራዋይ ወደ ትግራይ ክልል አንዲገባ በህወሃት በኩል ከፍተኛ ቅስቀሳ ቢደረግም ተቀባይነት አላገኘም።

በርካታ የትግራይ ተወላጆች በከተማው እንደሚኖሩ ገልጸው ማንኛውም የከተማዋ ነዋሪ የሚያገኘውን መሰረታዊ ፍላጎት ያለምንም አድሎና መገለል እያገኙ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

"ነገር ግን ጥቂት የህወሃት አመራሮች የራሳቸው ጥቅም ስለቀረባቸው ብቻ ረስተውት የኖሩትን የትግራይ ህዝብ መጠቀሚያ ለማድረግ ዛሬ ላይ በትኩረት እየሰሩ ነው" ብለዋል።

"የትግራይ ህዝብ የህወሃት አመራሮች ሴራ ስለገባው አካሄዳቸውን አይከተልም'' ያሉት መምህር ሀብቶም "በክልሉ ውስጥ በጭቆና ለሚኖረው ህዝብ የፌዴራል መንግስት ሊደርስለት ይገባል" ብለዋል።

ቀደምት የትግራይ አባቶች በኢትዮጵያዊነታቸው የማይደራሩና ለኢትዮጵያ ዋጋ የከፈሉ እንደሆኑ የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ልእልተ ሀይሌ ናቸው።

ለዘመናት ብቻቸውን ሲበሉ ኑሮው ዛሬ ላይ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚኖረውን የትግራይ ህዝብ በሰላም ከሚኖርበት አካባቢ ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ ከሌላው ወገኑ እንዲለያይ የህወሃት አመራሮች እየሰሩ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

ጥቂት ጥቅመኛ የህወሃት ፖለቲከኞች በትግራይ ህዝብ ላይ የተለየ አደጋ የተደቀነ አስመስለው እየሰበኩ መሆናቸውን የገለጹት ወይዘሮዋ "የፌዴራል መንግስት እስከታች ድረስ በመውረድ የትግራይን ህዝብ ማወያየትና ፍላጎቱን መረዳት ይኖርበታል" ሲሉም አመልክተዋል።

"በትግራይ ህዝብ ላይ የተለየ ችግር የተደቀነ በማስመሰልና ብልጽግና ፓርቲን አሃዳዊና የፌዴራሊዝም ጸር አስመስለው የሚሰበኩ የህወሃት አመራሮችን የውሸት ፕሮፖጋንዳ ለመከላከል የትግራይ ህዝብ በጋራ ሊሰራ ይገባል" ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የሴክተር ተቋማት ማስተባበሪያ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሃፍታይ ገብረእግዚአብሄር ናቸው።

መድረኩን የመሩት አቶ ሃፍታይ እንደተናገሩት የብልጽግና ፓርቲ የመላ ኢትዮጵያዊያንን ብልጽግናና እኩልነትን ለማረጋገጥ የሚሰራ ድርጅት ነው።

"የትግራይ ህዝብም ባረጀ የፖለቲካ አስተሳሰብ ሳይሆን ወቅቱን በሚዋጅና ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ተጠቃሚ በሚያደርግ አስተሳሰብ መታቃፍና ተጠቃሚ መሆን አለበት" ብለዋል።

የህወሃት አመራሮች ዛሬ ላይ ጸረ ኢትዮጵያና አህዳዊ አድርገው የሚገልጹት የብልጽግና ፓርቲ ሁሉንም የሃገሪቱን ህዝቦች እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው አወያይ በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የብልጽግና ፓርቲ አመራር ዶክተር ሙሉቀን ሃብቱ ናቸው።

"ዛሬ ላይ ህገ መንግስቱን በመጣስ በራሱ ሃሳብ በመጓዝ ላይ ያለው ህገ-ወጥ ቡድን ለተግራይ ህዝብ ተቆርቋሪ በመምሰል እያራመደ ያለው ፕሮፖጋንዳ ከእወነት የራቀና የብልጽግናን ሃሳብ ፈፅሞ ያልተገነዘበ ነው" ብለዋል።

"የብልጽግና ፓርቲ መላ ኢትዮጵያዊያንን በፖለቲካ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሰራና የትግራይ ህዝብን መሰረታዊ ችግር ለመፍታት የተቋቋመ ፓርቲ ነው" ሲሉም አብራርተዋል።

በባህር ዳር ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ለውጡ ለመላ ኢትዮጵያዊያን የመጣ መሆኑን ተረድተው ለጋራ ጥቅም የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸው የተናገሩት ደግሞ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ጽፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተመስገን በላቸው ናቸው።

በከተማው የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ያለምንም ስጋት መኖርና ለሀገራቸው አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ገልፀዋል።

በቀጣይ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሞ ውይይቱ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም