ቀጥታ፡

በሶማሌ ክልል የተገነባው የቆሬሌ የፀሐይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ተመረቀ

መስከረም 28/2013(ኢዜአ) በሶማሌ ክልል በቆሬሌ  የገጠር  ከተማ  ከፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ ለማመንጨትና  ኅብረተሰቡን  ተጠቃሚ  ለማድረግ የተገነባው አነስተኛ የፀሐይ ኃይል  ማመንጫ ተመረቀ።

የፌደራልና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የተመረቀው የቆሬሌ የፀሐይ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለምርቃት መብቃቱን የየዉኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የውኃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢኒጂነር ስለሺ በቀለ መንግሥት የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ሽፋን ለማሳደግ ከፍተኛ  በጀት መድቦ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ያከናወነና እያከናወኑ መሆኑን  ገልጸዋል።

እሳካሁን በተከናወኑ የከፍተኛ የማስተላለፊያ መስመሮች፤ የማከፋፈያ ጣቢያዎች ፤ የመካከለኛና የዝቅተኛ ዲስትሪብዩሽን መስመሮች 7 ሺህ 426 ከተሞች፣ መንደሮችና የገጠር ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ መሆናቸውን  ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም በጅጅጋ- ደገሃቡርና በጎዴ- ቀብሪደሃር የማስተላለፊያና የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች አማካኝነት የደገሃቡርና የቀብሪደሃር ከተሞች የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎ ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

በቆሬሌ የገጠር ከተማ የተገነባው የአነስተኛ ግሪድ  የፀሐይ  ኃይል  የኤሌክትሪክ  ኃይል ማመንጫ 325  ኪሎዋት  የኤሌክትሪክ  ኃይል  ከፀሐይ  ማመንጨት የሚያስችል ነው፡፡

የኃይል ማመንጫው 467.4 ሺህ የአሜሪካን ዶላርና 4.3 ሚሊየን የኢትዮጵያ ብር ወጪ የተደረገበት ፕሮጀክት መሆኑን ሚኒስቴሩ አመልክቷል።

የቆሬሌ የገጠር ከተማ ኃይል ማመንጫ በሰባት የአገሪቱ ክልሎች 12 የሙከራ የገጠር ቀበሌዎችን ከአነስተኛ ግሪድ ፀሐይ ኤሌክትሪክ በማመንጨት ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ በዓለም ባንክ ፋይናንስና በአገር ውስጥ ገንዘብ እየተገነቡ ካሉ 12 ፕሮጀክቶች አንዱ መሆኑን ገልጿል።

ሚኒስቴሩ አያይዞም ቀሪዎቹ 11 ፕሮጀክቶች  በከፊል የተጠናቀቁና  እየተጠናቀቁ እንደሚገኙ አስታውቋል።

ሁሉም የማይክሮ ግሪድ ፀሐይ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ሲጠናቀቁ በድምሩ 3 ሺህ 800 ኪሎዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት አቅም እንዳላቸው ሚኒስቴሩ በፌስቡክ ገጹ አመልክቷል።

ኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን 45 በመቶ የኤሌክትሪክ ሽፋን በ2017 ዓ.ም ከታዳሽ ኃይል ምንጮች 65 በመቶውን ከግሪድና 35 በመቶውን ደግሞ ከግሪድ ውጭ የኃይል ተጠቃሚ በማድረግ ሀገር አቀፍ የኤሌክትሪክ ሽፋኑን 100 ፐርሰንት ለማድረስ እየሠራች እንደምትገኝ ሚኒስቴሩ አስረድቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም