ቀጥታ፡

ክፈለ ከተማው ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ 70 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ ነው

አዲስ አበባ መስከረም 28/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮልፌ ቀራንዮ ከፍለ ከተማ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 70 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የግድቡ ዋንጫ ወደ ክፍለ ከተማው መምጣትን ተከትሎ እስካሁን ድረስ 20 ሚሊዮን ብር ማስባሰቡንም ገልጿል።

ክፍለ ከተማው ገንዘቡን ለመሰብሰብ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሕዳሴው ግድብ ዋንጫ ወደክፍለ ከተማው መምጣቱን መምጣቱን ተከትሎ ነው።

የሕዳሴውን ግደብ ዋንጫ ትናንት ከጉለሌ ከፍለ ከተማ የተረከበ ሲሆን ዋንጫውን በክፍለ ከተማው በሚገኙ 15 ወረዳዎች በማዘዋወር በህዝብ ንቅናቄ የታቀደውን ገንዘብ ለማስገባት እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።

የክፍለ ከተማው ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚና የሰው ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አባወይ ዮሐንስ የሕዳሴው ግድብ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀብት መሆኑን ጠቅሰው፣ ግድቡ ለፍጻሜ እንዲበቃ ክፍለ ከተማው የድርሻውን ለመወጣት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም የታቀደውን 70 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ በባንኮች፣ በክፈለ ከተማው ግቢ ውስጥና በተለያዩ አደባባዮች ቦንድ የመሸጥና ገንዘብ የማሰባሰብ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል።

ዕቅዱ እንዲሳካም የሕዳሴ ግድብ ዋንጫ ወደ ክፍለ ከተማው ከመግባቱ በፊት 20 ሚሊዮን ብር አስቀድሞ መሰብሰቡንም አቶ አባወይ ተናግረዋል፡፡

ይህም ለመሰብሰብ የታቀደውን ገንዘብ ማሳካት እንደሚቻል ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው ዋንጫው በክፍለ ከተማው የተለያዩ ወረዳዎች ለ10 ቀናት በማዘዋወር ገቢ የማሰባሰብ ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ባለሀብቶች፣ ድርጅቶችና መላው የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የጋራ ሀብት መሆኑን ተረድተው የሚችሉትን ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የሕዳሴው ግድብ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባለፈ የአንድነትና የብሮነት መገለጫ መሆኑን ያስገነዘቡት አቶ አባወይ፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

ዕቅዱ እንዲሳካ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግስት ሠራተኛውና ማህበራት የድርሻቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም