ቀጥታ፡

በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት የተገነባ ትምህርት ቤት ተመረቀ

ደሴ መስከረም 28/2013(ኢዜአ) የቀዳማዊት እመቤት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽህፈት ቤት ባደረገው 21 ሚሊዮን ብር ወጪ በደቡብ ወሎ ዞን አልብኮ ወረዳ የተገነባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዛሬ ተመረቀ። 

በምረቃው ስነ-ስርዓት ወቅት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እንዳሉት ሀገር ለመገንባት ቅድሚያ የተማረ የሰው ኃይል ሀብት ያስፈልጋል።

በሀገሪቱ ባለው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ክፍተት በሴቶች ላይ ያለውን ጫና ለማቃለል ጽህፈት ቤታቸው የሚካሄደው ስራ  አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ይህ ትምህርት ቤት በተደረገለት ድጋፍ ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱም መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፍ አለ በበኩላቸው በክልሉ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እጥረት ምክንያት ብዛት ያላቸው ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንደሚያቋረጡ ተናግረዋል።

የቀደማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት የክልሉን ክፍተት በመገንዘብ የተለያዩ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ለአገልግሎት እንዲበቁ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በተደረገው የገንዘብ ድጋፍም አራት ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ  መሆኑን ጠቅሰው ሁለቱ ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት መዘጋጀታቸውንና ቀሪዎቹ በሂደት ላይ እንደሚገኙ አሰረድተዋል።

ትምህርት ቤቶች በወቅቱ እንዲጠናቀቁ ቀዳማዊት እመቤቷ ያደረጉት ድጋፍና ክትትልም ለተቋማቱ በወቅቱ መጠናቀው ሚናቸው የጎላ እንደሆነ ገልፀዋል።

የአልብኮ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይማም ሰይድ እንዳመለከቱት ከዚህ በፊት በወረዳው  የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ  ተማሪዎች ከአካባቢው ርቀው ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ሃርቡና ከሚሴ ሄደው ለመማር በመገደድ ይቸገሩ ነበር።

ችግሩን ለማቃለል በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው  ጽህፈት ቤት ድጋፍ " በጦሳ ፈላና '' ትምህርት ቤቱ ተገንብቶ ለአገልግሎት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ትምህርት ቤቱ 18 የመማሪያ ክፍሎችና ሌሎችም ለመማር መስተማር ስራ  የሚያገለግሉ  ህንፃዎች እንደተሟሉለትና  ከአንድ ሺህ በላይ ተማሪዎችን ማስተናገድ እንደሚችል አስታውቀዋል።

የዘመኑን የትምህርት ስራ ለማስጀመር አስፈላጊ የመማሪያ ቁሳቁሶች በማሟላት የዘጠነኛና አስረኛ  ክፍል ተማሪዎችን ምዝገባ መጀመሩን ጠቁመዋል።

ከአከባቢው ነዋሪዎች መካከል  አቶ አማረ አሰፋ  በሰጡት አሰተያየተ ቀደም ሲል  በአካባቢው ትምህርት ቤት ባለመኖሩ   በርካታ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ያቋርጡ እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን ለልጆቻችን ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ ተደስተናል ብለዋል።

በምረቃ ስነ- ስርዓት የፌደራል፣ የክልልና የዞኑ እንዲሁም የወረዳው አመራሮችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም