ኮሮናን በመከላከል ትምህርት ለመጀመር መዘጋጃታቸውን ወለጋና ሰላሌ ዩኒቨርሲቲዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሮናን በመከላከል ትምህርት ለመጀመር መዘጋጃታቸውን ወለጋና ሰላሌ ዩኒቨርሲቲዎች ገለጹ
ነቀምቴ/ፍቼ / መስከረም 28/2013(ኢዜአ) በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተቋርጦ የቆየውን የመማር ማስተማር ሥራ ለመጀመር የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማከናወናቸውን ወለጋና ሰላሌ ዩኒቨርሲቲዎች ገለጹ፡፡
የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሐሰን ዩሱፍ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ተመራቂ ተማሪዎችን ቀድሞ በመቀበል የክለሳና መደበኛ ትምህርት ለመስጠት አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን አስታውቃል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች መኝታ፣ የምግብ፣ የጤና፣ የመዝናኛ፣ የመማሪያ ክፍሎችና ቤተ መፃሕፍትን ጨምሮ ተማሪዎች በበቂ ሁኔታ አግልግሎት መመቻቸቱን አመልክተዋል፡፡
የኮሮና ቫይሬስ ስርጭትን ለመከላከል የሚያገለግሉ ግብዓቶች እንደ ማስክ፣ ሳኒታይዘርና የእጅ መታጠቢያ ቦታዎችና ሌሎችም ለመማር ማስተማሩን ስራ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የመማር ማስተማር ሥራ ለማስጀመር እያደረገ ያለውን ዝግጅት ለመገምገም ከሚኒስቴሩ ባለሙያዎች በቦታው ተገኝተዋል።
በግምገማው የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የምርምርና የሥነ ምግባር ዳይሬክተር ዶክተር ዳንኤል ታደሰ መንግሥትና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አሁን ያለውን የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት ዪኒቨርሲቲዎች ኮሮናን እየተከላከሉ የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዲቀጥል ተወስኗል ብለዋል።
በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ከዩኒቨርሲቲው አመራር ጋር መክረዋል።
በዚህም ዩኒቨርሲቲው በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ተማሪዎችን በመቀበል የመማር ማስተማሩን ስራ ለማስጀመር በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
በተመሳሳይ የሰላሌ ዩኒቨርስቲ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር ወረርሽኙን ለመከላከል የተቀመጠውን መመሪያ ተከትሎ ተማሪዎችን ደረጃ በደረጃ ለመቀበል የሚያስችለውን የቁሳቁስ፣ የሰው ኃይልና የአሰራር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የዩኒቨርስቲው የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር ዶክተር የሺመቤት ቦጋለ ገልፀዋል፡፡
በተለይም ተማሪዎች ርቀቸውን ጠብቀው የመማር ማስተማር ስራን እንዲከታተሉ የሚረዳ የመማሪያ፣ የመመገቢያና የመኝታ ስፍራዎችን በበቂ ሁኔታ የማዘጋጀት ስራ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር በቅርቡ ለግምገማ የመጣው ሉኡካን በዩኒቨርስቲው የተለያዩ ግቢዎች ጉብኝት በማድረግ ቫይረሱን በመከላከል ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል ምክረ ሀሳብ መስጠታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም በአበበች ጐበና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የተቋቋመው የኮሮና መመርመሪያ ላብራቶር ከተማሪዎችና መምህራን ተነጥሎ በራሱ ግቢ እንዲንቀሳቀስ ተወስኗል ብለዋል፡፡
በአንዳንድ ሰራተኞችና መምህራን የሚታየው የቸልተኝነትና ጥንቃቄ ክፍተት እንዲስተካከል በቀረበው ሀሳብ መሰረትም እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡