ቀጥታ፡

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችላቸው ቁመና ላይ ናቸው - የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27/2013 ( ኢዜአ)ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችላቸው ቁመና ላይ መሆናቸውን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። 

ሚኒስቴሩ የ2013 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የስራ አፈፃፀም ላይ መግለጫ ሰጥቷል።

ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ አብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝንና ሠላማዊ የመማር ማስተማርን ከግምት ያስገባ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በቀጣዩ አንድ ሣምንት ውስጥ የተማሪ ቅበላ ዝግጅታቸውን እንደሚያጠናቅቁም አስታውቀዋል።

በሩብ ዓመቱ በርካታ ስራዎች መሰራታቸው የተጠቀሰ ሲሆን ዩኒቨርሲቲዎቹ በችግኝ ተከላና በሌሎች አገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳትፎ ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል።

ከዚህም ውስጥ ለ'ገበታ ለሃገር' ፕሮጀክት 100 ሚሊዮን፣ በጎርፍ ለተጎዱ ዜጎች መቋቋሚያ 20 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።

ሚኒስትሩ ኮቪድ-19ን እየተከላከሉና ሠላምን በጠበቀ መልኩ ትምህርት ማስቀጠል የሚያስችሉ መመሪያዎች መውጣታቸውን ገልፀዋል።

የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ የግል ተቋማትና የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎችም በመመሪያው መሰረት በቂ ዝግጅት ማድረጋቸው እየታየ ትምህርት እንደሚጀምሩም ታውቋል።

ብዙሃኑ ዩኒቨርሲቲዎች ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ሚኒስቴሩ ማረጋገጡንና ከበሽታና ከግጭት ነፃ የሆነ መማር ማስተማር እንዲኖር ግብረ ኃይል መቋቋሙ ተገልጿል።

ለዩኒቨርሲቲዎቹ የወጣው መመሪያ ሙቀት ከመለካት ጀምሮ የተማሪዎችና የመምህራን የትምህርት እንቅስቃሴና አገልግሎት አሰጣጥን የሚመለከት መሆኑንም ተናግረዋል።

ተማሪዎች በበሽታው እንዳይያዙ ከማድረግ ጀምሮ ምልክት የታየባቸው ተማሪዎች ክትትል የሚያደርጉበት አሰራርና ምቹ ሁኔታም ተዘጋጅቷል ብለዋል።

ሠላምና ፀጥታን በተመለከተ ሁሉም ተቋማት ትኩረት የሰጡት መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ ጥብቅ መመሪያ መውጣቱን አስታውቀዋል።

አያይዘውም የተማሪዎች ቤተሰቦች ልጆቻቸውን በስነ-ልቦና እንዲያዘጋጁ፣ ከትምህርታቸው ውጭ በሆኑ ጉዳዮች እንዳይገቡና ለግጭት ምክንያት እንዳይሆኑ መምከር እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በትግራይ ክልል ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተያይዞ ከጋዜጠኞች ለቀረቡ ጥያቄዎች ሚኒስትሩ ዩኒቨርሲቲዎች ከማንኛውም የፖለቲካ አመለካከት ነፃ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በመሆኑም ከየትኛውም ክልል ወደ ትግራይ፤ ወይንም ከትግራይ ወደ የትኛውም ክልል ዩኒቨርሲቲ ሄደው የሚማሩ ይሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም