ቀጥታ፡

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዝከረ መስፍን ወልደ ማሪያም መረሃ-ግብር ተካሄደ

ባህር ዳር መስከረም 27/2013(ኢዜአ) በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ማምሻውን ዝከረ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማሪያም መረሃ-ግብር ተካሂደ። 

በመረሃ ግብሩ ስነስርዓት በዩኒቨርሲቲው የህብረተሰብ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር አረጋ ባዘዘው ባቀረቡት ጹሁፍ እንዳመለከቱት  ፕሮፌሰር መስፍን ከንጉሱ እስከ ኢህአዴግ ዘመን ድረስ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ጥቅም ሲሞግቱና ሲከራከሩ የነበሩ ታላቅ ምሁር ነበሩ።

ፕሮፌሰር መስፍን ለነዋይና ስልጣን እራሳቸውን ያላስገዙ ከግልሰቦች ጋር ሳይሆን ከስርአት ጋር በእውቀትና በምክንያታዊነት ሲሟገቱ የኖሩ የሰብአዊ መብት ተሟጋችና የኢትዮጵያ ጠበቃ እንደነበሩም አውስተዋል።

ለአመኑበት ዓላማና ኢትዮጵያዊያንን ይጠቅማል ብለው ላሰቡበት ነገር ሁሉ በድብቅ ሳይሆን በአደባባይ የመሪዎችን ሃሳብ የሚሞግቱና በድፈረት የሚገስጹ ታላቅ ኢትዮጵያዊ እንደነበሩም ጠቅሰዋል።

’"ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ዝናን የማይወዱና በግልጽ የሚናገሩ የአደባባይ ምሁር ነበሩ’’ ያሉት ደግሞ ሌለኛው ጹሁፍ አቅራቢ የዩኒቨርሲቲው የታሪክ መምህር ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ ናቸው።

ፕሮፌሰር መስፍን ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የማይደራደሩና ግለሰቦችን ሳይሆን ስርዓትን በድፍረት የሚሞግቱ ደፋር የብእር አርበኛ እንደነበሩም ጠቅሰዋል።

የደርግ ጭካኔ ያላሸነፋቸው ጽኑ ኢትዮጵያዊ  እንደነበሩ አመልክተው ፤በጎሳ ፖለቲካ ምክንያት ኢትዮጵያን አደጋ ላይ ጥሏት የነበረውን የህወሓት/ ኢህአዴግን መንግስትም በድፍረት ሲሟገቱ ኑረዋል ብለዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለረጅም ዓመታት ባስተማሩበት የህብረተሰብ ሳይንስ ትምህረት ተማሪዎቻቸውን ግብረ ገብነትና የኢትዮጵያን ታሪክን በተጓዳኝ በማሰረዳት እንደሚታወቁም ጠቁመዋል።

ዶክተር ጥጋብ በዜ በበኩላቸወ ''ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ይጠቅማል ብለው የሚያምኑበትን ሁሉ በአደባባይ የተናገሩና የሞገቱ የጨለማ ብረሃን የነበሩ ምሁር ናቸው'' ብለዋል።

ሁለገብ ምሁርና ጽኑ ኢትዮጵያዊ ነበሩ ያሉት ዶክተር ጥጋብ ያሳተሟቸው በርካታ መጽሃፍትና የምርምር ስራዎች ለትውልዱ ህያው ምስክሮች መሆናቸውን አመልክተዋል።

ከምሁር የሚጠበቅ ድፍረትና የሚሰማን ነገር በግልጽና በአደባባይ በመናገር ፋና ወጊ ኢትዮጵያዊ እንደነበሩም አብራርተዋል።

በመረሃ-ግብሩ  የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አመራሮችና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን ባደረባቸው ህመም  በሕክምና ሲረዱ ቆይተው መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም በ90 ዓመታቸው ማረፋቸውና የቀብራቸውም ስነ-ስርዓት መስከረም 26/2013ዓ.ም በአዲስ አበባ ቅድስት ስላሴ ካቴድራል መፈጸሙን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም