ቀጥታ፡

በደቡብ ክልል ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሕፃናትን ተደራሽ የሚያደርግ የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ተጀመረ

ሀዋሳ፣ መስከረም 27/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ቀናት የሚካሄድና ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሕፃናትን ተደራሽ የሚያደርግ የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ተጀመረ።

የክልሉ ጤና ቢሮ በከንባታ ጠምባሮ ዞን ሺንሺቾ ከተማ እስከ መስከረም 30/ 2013 ዓ.ም የሚካሄደውን የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ማስጀመሪያ መርሀ-ግብር አካሂዷል።

በዚህ ወቅት የጤና ቢሮው ኃላፊ አቶ አቅናው ካውዛ እንዳሉት በክትባት ዘመቻው ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሁለት ሚሊዮን 100 ሺህ  ሕፃናት ተጠቃሚ ይሆናሉ።

በክልሉ ዘመቻው ተደራሽ የሚሆነው በ11 ዞኖችና ሰባት ልዩ ወረዳዎች መሆኑን አስታውቀዋል።

የክትባት ዘመቻውን ለማስፈጸም የቅድመ ዝግጅት ሥራ መከናወኑን አመልክተው፤ ለዚህም የባለሙያዎች ሥልጠና መሰጠቱንና አስፈላጊው ግብዐት ወደ የአካባቢው ቀርቧል ብለዋል።

ዘመቻውን የሚያካሄዱ የህክምና ባለሙያዎችና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በመቀናጀት እንደሚያከናውኑ አስረድተዋል።

ቤት ለቤት በሚካሄደው የክትባት ዘመቻ ጋር የኮሮና  ወረርሽኝ የመከላከል ሥራ በተጓዳኝ እንደሚከናወን የተናገሩት ኃላፊው፤ የምግብ እጥረት ያለባቸው ሕፃናትን እንዲሁም ሌሎች ተከታታይ ክትባቶችን ያልወሰዱ ሕፃናትን የመለየት ሥራም  ይሰራል ብለዋል።

የከንባታ ጠምባሮ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ መልካሙ ገብሬ በበኩላቸው መምሪያው ዘመቻውን የተሳካ ለማድረግ በየደረጃው ካሉ የአመራር አካላት ጋር በመቀናጀት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል።

ግብአቶችንና የሰው ኃይል ከማሟላት ባለፈም የማህበረሰብ ሬዲዮን ጨምሮ የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን  በመጠቀም ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥና የመቀስቀስ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።

በዞኑ  አስር  ወረዳዎች ከ153 ሺህ በላይ ሕፃናት የክትባቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡

በዘመቻው ማስመጀሪያ መርሀ-ግብሩ ላይ ተገኝተው ልጃቸውን ካስከተቡ እናቶች መካከል ወይዘሮ ሰራዊት ወልደሰንበት በሰጡት አስተያየት በቀበሌያቸው በነበረው የቅስቀሳ ሥራ መረጃ በማግኘታቸው ልጃቸውን ለማስከተብ እንደመጡ ተናግረዋል።

በአካባቢያቸው በበሽታው የተጎዱ ሰዎችን  አልፎ አልፎ  እንደሚመለከቱ የተናገሩት ወይዘሮ ሰራዊት ልጃቸው ለበሽታው እንዳይጋለጥ በማሰብ ማስከተባቸውን ገልጸዋል።

እናቶች የባለሙያዎችን ምክር መስማትና ፖሊዮንም ሆነ ሌሎች በሽታዎች መከላከያ ክትባቶችን በመከታተል ማስከተብ እንደሚጠበቅባቸውም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም