ረጲ ከደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ከዕቅዱ በላይ ኃይል አመንጭቷል -- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል - ኢዜአ አማርኛ
ረጲ ከደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ከዕቅዱ በላይ ኃይል አመንጭቷል -- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል
አዲስ አበባ መስከረም 27 / 2013 (ኢዜአ) የረጲ ከደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በ2012 ዓ.ም ከታቀደው በላይ ኃይል ማመንጨቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
ረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የአዲስ አበባን ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ለማዘመንና ከደረቅ ቆሻሻ ኃይል ለማመንጨት ግንባታው በ2006 ዓ.ም መጀመሩ ይታወሳል።
የፕሮጀክቱ ግንባታ በ2010 ዓ.ም ተጠናቆ ለምረቃ የበቃ ሲሆን የሙከራና የፍተሻ ሥራው ተጠናቆ መጋቢት 2011 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ወደ ኃይል ማመንጨት ሥራ ገብቷል።
የኢትዮጵያ አሌክትሪክ ኃይል የሕዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬተር አቶ ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት ጣቢያው በ2012 ዓ.ም ከታቀደው በላይ ኃይል ማመንጨት ችሏል።
"2011 ግማሽ ዓመትን ወደዚህ ይዞ ከተመረቀና ስራ ከጀመረ በኋላ በዓመቱ መጨረሻ ላይ ከታሰበው በላይ ኢነርጂ ማመንጨት የቻለ ጣቢያ ነው"ብለዋል ።
2012 ላይ 179 ነጥብ 2 ጊጋ ዋት ሠዓት ኢነርጂ የዓመቱ አማካይ ምርት ነው ይህን ማምረት ችሏል ያሉት አቶ ሞገስ ከክንውኑ አንጻር የ29 ነጥብ 85 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ይሄም ከዕቅዱ በላይ የ20 ፐርሰንት ጭማሪ ያሳየ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ነው።
ከየትኛውም አቅጣጫ የሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት ገብቶ ወደሚፈለግበት አካባቢ የሚሰራጭ መሆኑን የገለጹት አቶ ሞገስ የረጲ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በአገሪቷ የኃይል አቅርቦት የነበረው ድርሻ ቀላል የሚባል አለመሆኑን አንስተዋል።
ከቆሻሻ ጋር የሚቀላቀሉና በቀላሉ ሊቃጠሉ የማይችሉ ባዕድ ነገሮች ጣቢያው በሙከራና ፍተሻ እንዲሁም በሙሉ አቅሙ ማምረት በጀመረ ጊዜ ያጋጥም የነበረ ችግር መሆኑን ዳይሬክተሩ አውስተዋል።
ይህም ቆሻሻውን ለማቃጠል የሚወጣውን ወጪ ከመጨመር ባለፈ የሚመነጨው ኃይል እንዲቀንስ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ይሁንና የከተማ አስተዳደሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ለችግሩ መፍትሄ መስጠቱን አቶ ሞገስ ገልጸዋል።
በአፍሪካ የመጀመሪያ ነው ለተባለለት የረጲ ከደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ግንባታ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወጪ ሆኗል።
ፕሮጀክቱ ከኃይል ማመንጨት ባሻገር የአዲስ አበባን የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ማዘመንን ታሳቢ አድርጎ ወደ ስራ የገባ ሲሆን በቀን በአማካይ 1 ሺህ 400 ቶን ቆሻሻ የማስወገድ አቅም አለው።