ቀጥታ፡

ኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የተቋማትን የአቅም ውስንነት ችግር ለመፍታት መስራት አለበት--ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ

አዳማ፣መስከረም 27/2013 (ኢዜአ) ኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በክልሉ በመንግስታዊ ተቋማት የሚታየውን የአቅም ውስንነት ችግር ለመፍታት በትኩረት መስራት እንዳለበት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ማዕከል ግንባታ አስተባባሪና የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ አሳሰቡ።

ዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ በአራት የትምህርት ፕሮግራሞች የዶክቶሬት ዲግሪ ትምህርት ሊጀምር ነው።

በአዳማ እየተካሄደ ባለው የስርዓተ ትምህርት ክለሳ አውደ ጥናት መድረክ የተገኙት ዶክተር ቢቂላ  እንደገለጹት ለሀገራዊ ሪፎርሙ ፈታኝ የሆነው በመንግስታዊ ተቋማት የሚታየው የአቅም ውስንነት ነው።

የእውቀት፣ አመለካከትና ክህሎት ችግር የመንግስታዊ ተቋማት ፈፃሚዎችና አመራሮች ዘንድ በስፋት የሚታይ ማነቆ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሰው ኃይሉን አቅም ለመገንባት በስቴት ዩኒቨርሲቲው የተጀመሩ ፕሮግራሞች የላቀ ሚና አላቸው ብለዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት ሲተገበሩ በቆዩት የሪፎርም ስራዎች ትልቁ ክፍተት የነበረው የመንግስት ተቋማት የመፈጸም ውስንነቶች ናቸው፤ ይህ የመፈጸም አቅም ውስንነት ደግሞ በሰው ኃይላችን ላይ ከሚታየው የእውቀት ክህሎትና አመለካከት ድክመት ይመነጫል፤ በመሆኑም የሰው ኃይልን ጥራትና ቁርጠኝነት መገንባት የሀገሪቱን  ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ለማሳካት ቁልፉ እንደሆነ አምናለሁ ነው ያሉት ዶ/ር ብቂላ።

የሚከፈቱት የትምህርት ፕሮግራሞች ዓላማ ክልሉም ብሎም ሀገሪቱ ከደረሰችበት ልማትና እድገት ጋር መራመድ የሚችል፣ የመፈፀምና ማስፈፀም አቅም ብቃቱ የተረጋገጠ የሰው ኃይል እንዲኖር ለማስቻል ነው ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው እስካሁን መካክለኛና ከፍተኛ አመራሮችን በአጫጭርና ረዥም ጊዜ ስልጠናዎችን በመስጠት አቅም ለማሳደግ  እየሰራ ቢሆንም ብቃትን ከማሳደግ አንፃር የትምህርትና ስልጠና ስርዓቱን በመከለስ አሁንም በሙሉ አቅሙ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።

አሁን በክልሉም ሆነ ሀገር ደረጃ የተጀመረውን ተቋማዊ አሰራር፣ አደረጃጀትና አቅም ግንባታ የሪፎርሙ ትኩረት በመሆናቸው ዩኒቨርስቲው በትኩረት ሊሰራባቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ገመቹ አራርሳ በበኩላቸው የመንግስት ሰራተኛውን በእውቀትና  ክህሎት አቅሙን  ለማሳደግ እየሰራን ነው ብለዋል።

በዚህም ብቁ፣ ተወዳዳሪና ውጤታማ የሆነ የሰው ኃይል በሁሉም መንግስታዊ መዋቅር ለመፍጠር የሚያስችል የትምህርትና ስልጠና ፕሮግራም ቀርጸው እያስተማሩ  መሆናቸውን አመልክተዋል።

አሁንም በክልሉ መንግስት ፍላጎት ላይ በመመስረት በፌዴራልዝምና መንግስታዊ ጥናት፣ በህዝብ አስተዳደርና ፖሊስ ጥናት፣ በአመራርና አስተዳደር እንዲሁም በልማታዊ ጥናት ፕሮግራሞች  የዶክቶሬት ድግሪ ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።

በሁለተኛ ዲግሪ የሚከፈቱ ሌሎችም ፕሮግራሞች እንደሚኖሩ አመልክተዋል።

በእውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት ብቁ የሆነ የመንግስት ሰራተኛን በመፍጠሩ እንዲሁም በተመራማሪዎች፣ አማካሪዎችና ፖሊሲ አውጭዎች  በኩል ያለውን የክልላዊ መንግስቱን ፍላጎት በመንተራስ ተግባራዊ ተሞክሮዎች እንደነበሩ በመግለጽ አሁንም የስርዓተ ትምህርት  ክለሳው ይህኑ መሰረት ያደረገ መሆኑን ተናግረል።

ለአብነትም በኮምፒዩተር ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን በሁለተኛ ዲግሪ  እንዲሁም በአራት የትምህርት ዓይነቶች ደግሞ የሶስተኛ ድግሪ ሊጀመር መሆኑንም ገልጸዋል።

በክልሉ የመንግስት ሰራተኛው  ቁጥር እያደገ ቢመጣም ህብረተሰቡ ጥራት ያለው ቀልጠፋ አገልግሎት  እያገኘ አይደለም ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙሉነህ ሄደቶ ናቸው።

በዚህም የህዝብ ቅሬታ እየጨመረ መሆኑን ገልጸው የትምህርት ፕሮግራሞቹ መጀመር በመንግስታዊ ተቋማት ያለውን ውስብስብ ችግር ለማስወገድ ቁልፍ ሚና እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።

ዶክተር ሙሉነህ በአሁኑ ወቅት ከ54 የኦሮሚያ ቢሮዎች የቀረቡ አቅም የሚጠይቁ ጥያቄዎች አሉ፤ ይህን ጥያቄ ለማስተናገድ ብቁ የሰው ኃይልና ተመራማሪዎች ያስፈልጋል ብለዋል።

የስርዓተ ትምህርት ክለሳ አውደ ጥናቱ መድረክ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ምርምር ተቋማት የተወጣጡ ምሁራን እየተሳተፉ ነው።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም