ለወጣቶች የስራ እድል የመፍጠር ጉዳይ ቅድሚያ እና ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ስራ ነው" -- ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ለወጣቶች የስራ እድል የመፍጠር ጉዳይ ቅድሚያ እና ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ስራ ነው" -- ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ

መስከረም 27/2013 (ኢዜአ) አመራሩ ለስራ እድል ፈጠራ ዘርፍ ቅድሚያ በመስጠት በልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የስራ እድል ፈጠራ ምክር ቤት በ2013 በጀት ዓመት የስራ እድል ፈጠራ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እና የክፍለ ከተሞች ስራ አስፈጻሚዎች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
በስራ እድል ፈጠራ ምክር ቤት ላይ የተገኙት ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለሴቶች እና ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠር የከተማዋን ኢኮኖሚያዊ ፣ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን በማፋጠን ረገድ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
በከተማዋ ያልተነካ ሰፊ የስራ ዕድል መኖሩን የጠቀሱት ምክትል ከንቲባዋ ስራን እና ስራ ፈላጊ ዜጎችን በማቀራረብ በኩል ብዙ ክፍተቶች መኖራቸው ገልጸዋል፡፡
በዚህም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ለስራ እድል ፈጠራ ዘርፍ ከእቅድ ጀምሮ እስከ አፈጻጸሙ ድረስ ቅድሚያ በመስጠት በልዩ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ወይዘሮ አዳነች ተናግረዋል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት ለስራ ፈጠራ ተብለው የተበተኑ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ የብድር ገንዘብ በወቅቱ እንዲመለስ በማድረግ ለቀጣይ ወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ መልሶ ማበደር መቻል አለበት ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በመስሪያ ሼዶች አካባቢ የሚስተዋሉ የመብራት አቅርቦት እና የመሰረተ ልማት ችግሮች በአፋጣኝ እንዲፈቱ ወይዘሮ አዳነች አሳስበዋል፡፡
የስራ እድል ፈጠራ ምክር ቤቱ የ2013 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከማዕከል እስከ ክፍለ ከተማ የተሰሩ ስራዎች አፈጻጸም ሪፖርት የተገመገመ ሲሆን በዘርፉ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና የቀጣይ የስራ አቅጣጫ ዙሪያ ሰፊ ምክክር ተካሂዷል፡፡
(የአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክረተሪ)