የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ገበያ መረጃ አገልገሎቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ሊያደርግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ገበያ መረጃ አገልገሎቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ሊያደርግ ነው

አዲስ አበባ፣መስከረም 27/2013 (ኢዜአ) የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ገበያ መረጃና ህዝባዊ አገልገሎቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ሊያደርግ ነው።
ሚኒስቴሩ አሰራሩን ዲጅታላይዝ ለማድረግ የሚያስችለውን ስምምነት ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ተፈራርሟል።
የመግባቢያ ሰነዱን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ በዛሬው እለት ተፈራርመዋል።
በስምምነቱ መሰረት አሰራሩ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለማድረስና ዲጂታል የስራ ገበያ መረጃ ስርአት እውን ይሆናል።
አሰራሩ የስራ ፍላጎትን በቀላሉ ለመሰብሰብ፣ በቅጥር ወቅት የሚወጣ ወጭን ለመቀነስና ሌሎች ጠቀሜታዎች ይኖሩታልም ተብሏል።
በአገር ውስጥ የሚገኘውን የሰራተኛ ሃይል፣ የስራ ብዛት፣ የስራ አጥነት መረጃ፣ ተፈላጊ የስራ መደቦችና የክህሎት አይነት የያዘ የስራ ገበያ መረጃ እንዲኖር የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደገለጹት ስምምነቱ ዘመናዊ አሰራር እንዲዘረጋ በማድረግ በተቋሙ በመረጃ ዘርፍ የሚስተዋለውን ክፍተት ይሞላል።
የህዝብ አገልግሎትን ለማቀላጠፍና የስራ ገበያ መረጃን ለማዘመን ያግዛልም ነው ያሉት።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ፤ በስምምነቱ መሰረት የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አሰራሩን ለማዘመን የሚያስችሉ አሰራሮች እንደሚዘረጉ አብራርተዋል።
በስምምነቱ መሰረት ሁለቱ ተቋማት ያላቸውን ሃብትና ልምድ በጋራ ለመጠቀም ያስችላቸዋልም ነው ያሉት።
ብሔራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በ2012 ዓ.ም መጽደቁ ይታወሳል።
በስትራቴጂው የጋራ መግባባት በመፍጠር ብሔራዊ የሰራተኛ አስተዳደርንና ተያያዥ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት መጠቀም አስፈላጊ መሆኑ ተመለክቷል።