የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ለቱሪዝም ልማት አገልግሎት እንዲውል መስራት ይገባል- ዶክተር አብይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ለቱሪዝም ልማት አገልግሎት እንዲውል መስራት ይገባል- ዶክተር አብይ አህመድ
ባህር ዳር መስከረም 27/2013 (ኢዜአ) የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ለሀገሪቱ ከሚያስገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢ በተጨማሪ ለምርምርና ቱሪዝም ልማት አገልግሎት እንዲውል በትኩረት መስራት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምረቃ ስነ ሥርዓት ወቅት ባህርዳር በተፈጥሮ ውብ፣ ሳቢና ለምለም ከተማ ናት ብለዋል።
ከተማዋ ያላትን የተፈጥሮ ፀጋ በማልማት ለኢኮኖሚው አጋዥና ለሥራ እድል ፈጠራ ጭምር እንዲውል ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተለይም በቅርቡ በሃገር አቀፉ የገበታ ለሃገር ፕሮጀክት ግንባታው የሚካሄደው የጎርጎራ ፕሮጀክት ለባህር ዳር ከተማ ቱሪዝም እድገት የላቀ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።
የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ መገንባትም ለሃገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ከማስገኘት ባለፈም ለቱሪዝም እንቅስቃሴ፣ ለምርምርና እድገት ጠቀሜታ እንዲውልም በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።
እንዲሁም የቴክኖሎጂና እውቀት መፍለቂያና የመዝናኛ አገልግሎት እንዲሰጥም እንዲሁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ''ፓርኩን ሰዎች ካላዩት አይማሩበትም እየዘጋን ማደግ አንችልም፤ እየከፈትን፣ እየሰጠንና እየተቀበልን ማሳደግ ይገባል " ብለዋል።
ፓርኩ የአካባቢውን ማህበረሰብ ያቀፈ ልማት የሚፈጥር፣ ኑሮ የሚያሻሽልና የከተማዋን ውበት የሚያስጠብቅ እንዲሆን የሁላችንም ርብርብ ይጠይቃል ሲሉም ገልጸዋል።
አካባቢውን ከተለመደው የግብርና አሰራር በማላቀቅም ወደ ዘመናዊነት የሚቀይር ፈር ቀዳጅ በመሆኑም ለውጤታማነቱ በተደራጀ አግባብ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዱካን ደበበ በበኩላቸው ለሃገሪቱ ሁለንተናዊ ለውጥ የኢንዱስትሪ ዘርፉ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።
በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ውጤታማና በዓለም ገበያው ተወዳዳሪ ለማድረግ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ተናግረዋል።
በሃገሪቱ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች መገንባታቸውን ጠቅሰው፤ ከተገነቡት መካከልም አስሩ ወደ ማምረት መሸጋገራቸውን አስታውቀዋል።
ፓርኮቹ ለ76 ሺህ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል እንደፈጠሩ ገልጸው 160 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎችም በተዘዋዋሪ መንገድም ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንምጠቁመዋል።
የኮሮና ቫይረስን በሽታን በመከላከልም ፓርኮቹ ሰራተኞቻቸውን እንዳይቀንሱ ከማድረግ ባለፈ ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች 400 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ከውጭ ምንዛሬ ገቢ ባለፈም በቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያ ምዕራፍ በ75 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተገነቡት ስምንት ሸዶችም ለጨርቃጨርቅ እና "ጋርመንት " ለተሰማራ የውጭ ደርጅት መተላለፋቸውን አስታውቀዋል።
በፓርኩ ግንባታ በልማት የተነሱ የአካባቢው አርሶ አደሮችም በፓርኩ ግንባር ቀደም ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።
በሃገሪቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተጀመሩ ሁለንተናዊ የለውጥ ስራዎችን ለማሳካት ኢንዱስትሪ ፓርኮች የላቀ ሚና አላቸው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ናቸው።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች መገንባት የውጭ ባለሃብቶችን እውቀት፣ ካፒታል፣ ቴክኖሎጂና መሰል ልምዶችን በመቅሰም በዘርፉ ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ተወዳዳሪ ለመሆን እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
ከዚህ በተጓዳኝም የሃገር ውስጥ አቅምን አሟጦ ለመጠቀም ኢትዮጵያዊያን ባለሃብቶችን በመደገፍ ውጤታማ እንዲሆኑ በትኩረት ማገዝ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ውጤታማ እንዲሆንም የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግም አቶ ተመስገን አስታውቀዋል።
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጨምሮ ሌሎችም የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የኃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።
የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ለዶክተር አብይ አህመድ፣ ለአቶ ገዱ አንዳርጋቸውና ለአቶ ብናልፍ አንዷልም የካባ ሽልማት አበርክቷል።