የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን በአካባቢ ጥበቃና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን በአካባቢ ጥበቃና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ገለጸ
አዲስ አበባ፣መስከረም 27/2013 (ኢዜአ) የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን የአካባቢ ጥበቃና ቱሪዝምን ማዘመን የበኩሉን ሚና ለመወጣት መዘጋጀቱን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርና የቱሪዝም ኢትዮጵያ የቦርድ ሊቀመንበር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፓርኮች ለአካባቢው ነዋሪዎች ጥቅም እየሰጡ ጥበቃ እንዲደረግላቸው እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና ባለቤታቸው ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ በእናቶችና ህፃናት፣ በወጣቶች ፈጠራ እንዲሁም አካባቢ ጥበቃና ቱሪዝም ላይ ያተኮረ ኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን መመስረታቸው ይታወሳል።
አቶ ኃይለማርያም ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከዝቅተኛው ዳሎል እስከ ከፍተኛው ራስ ዳሽን ተራራ ባለ የተፈጥሮ ጸጋ የታደለች ናት።
ከቀደምት የግብጽ፣ ፐርሺያና ሮም ስልጣኔ ተርታ የምትሰለፍ በተፈጥሮ የበለጸገች ሀገር ብትሆንም የተፈጥሮ ሀብቶቿ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዳልዋሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ 22 ብሔራዊ ፓርኮች ቢኖሯትም አያያዛቸው ደካማ በመሆኑ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ በማድረግ የአካባቢ ጥበቃ ስራ መስራት አለመቻሉንም ገልጸዋል።
በመሆኑም ኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን ከተቋቋመባቸው ሶስት ምሰሶዎች አንዱ በሆነው የአካባቢ ጥበቃና ቱሪዝምን ማዘመን የበኩሉን ሚና ይወጣል ብለዋል።
የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ከኬንያና ታንዛኒያ ፓርኮች ቀጥሎ ሁለተኛው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአጥቢ እንስሳት ከቦታ ቦታ የሚዘዋወሩበት መሆኑን ገልጸዋል
የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ የመሰረተ ልማት ችግር ያለበት በመሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአጥቢ እንስሳት ወደ ደቡብ ሱዳን የሚሰደዱበት ትዕይንት መኖሩንም ገልጸዋል።
ኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን በፓርኮች ላይ ላለው መሰረታዊ ችግር መፍትሄ በመስጠት ኢትዮጵያ ከቱሪዝም የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ያደርጋል ብለዋል
ከጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ በተጨማሪ የኦሞና ማጎ ብሔራዊ ፓርኮች በአያያዝ ጉድለት የተራቆቱ ቢሆንም ምርጥ የሚባሉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ያሉ ፓርኮች ጉዳት በጥናት ተለይቶ ወደ ትክክለኛ ቁመናቸው እንዲመለሱ በመጀመሪያው ምዕራፍ ተይዘዋል ብለዋል።
በጋምቤላና ኦሞ ብሔራዊ ፓርኮች ላይ ያለውን ውስንነት መሰረት በማድረግ መርሃ ግብሮች ተቀርጸው ወደ ሥራ ገብተናልም ነው ያሉት።
የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክና ሌሎችም የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ለአካባቢው ማህበረሰብ ጥቅም እየሰጡ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ወደ ተግባር መገባቱንም ገልጸዋል።
ፋውንዴሽኑ ሁሉንም ፓርኮች ለጎብኝዎች ምቹ የማድረግ የረጅም ጊዜ እቅድ እንዳለውም አቶ ኃይለማርያም ተናግረዋል።