ቀጥታ፡

የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ላይ የሚመክር ጉባኤ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ መስከረም 27/2013(ኢዜአ) በኢትዮጵያ የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ላይ የሚመክር ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። 

በአፍሪካ ደረጃ የሚከበረው 'አፍሪካ አምነስቲ መንዝ' የተሰኘው ከሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር የፀዳ ወር በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተከበረም ይገኛል።

በጉባኤው የአፍሪካ ኅብረት ተወካይ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጄኔራል እንዳሻው ጣሰውና ሌሎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ታድመዋል።

የሠላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል "የሕዝቡን ሁለንተናዊ ደህንነት ለማረጋገጥ በዘመናዊ መንገድ የተደገፈ የሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ቁጥጥር ተጠናክሮ ይቀጥላል" ሲሉ ተናግረዋል።

"ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ በአፍሪካ ሠላምና ደህነንት ላይ ግጭትና ስጋት በመፍጠር ሕዝቡን ለከፋ ጉዳት እየዳረገ ነው" ሲሉም አክለዋል ሚኒስትሯ።

በጦር መሳሪያዎቹ በመታገዝ ከቀላል እስከ ከፍተኛ የሽብር ጥቃት የዘለቁ ወንጀሎች እየተፈፀሙ ስለመሆኑም ገልፀዋል።

የአፍሪካ ሀገራት የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ 2004 የፀደቀው የናይሮቢ ፕሮቶኮል መስራችና አባል ብትሆንም የጦር መሣሪያ ዝውውርና ቁጥጥር ብሔራዊ የሕግ ማዕቀፍ እንዳልነበራት ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ይሁንና በ2010 ዓ.ም የተካሄደውን ለውጥ ተከትሎ በተሰራው ጠንካራ ስራ የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ መውጣቱን ነው የገለጹት።

"ኃይል መጠቀም የመንግስት ኃላፊነት ብቻ ነው" ያሉት ሚኒስትሯ "የሕግ የበላይነትን በማስከበርና አዋጁን ተፈጻሚ በማድረግ የኀብረተሰቡን ደህንነት እናረጋግጣለን" ብለዋል።

ከዚህ ባለፈ የሕዝቡን ሁለንተናዊ ሠላምና ደህንነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ፤ ለዚህ ስኬትም ሕዝቡ ከመንግስት ጎን በመቆም ፀረ-ሠላም ኃይሎችን መታገል እንዳለበት አሳስበዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም በዜጎች ስነ-ምግባር እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የሠላም ሚኒስቴር ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠርና የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጁን ለማስተግበር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም