ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ "የገበታ ለሀገር" ፕሮጀክት የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለውጭ ባለሃብቶች አስተዋወቀ

አዲስ አበባ መስከረም  26/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን "የገበታ ለሀገር" ፕሮጀክት የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለውጭ ባለሃብቶች አስተዋወቀ፡፡

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት ባለሃብቶች በፕሮጀክቱ ያሉትን የኢንቨስትመንት አማራጮችን እንደሚያጤኗቸው ገልጸዋል፡፡

ለባለሃብቶቹም በፕሮጀክቱ በታቀፉት በጎርጎራ፣ በኮይሻና በወንጪያሉትን የኢንቨስትመንት ዕድሎችና ሊሰማሩባቸው በሚችሏቸው አማራጮች ላይ ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን የውይይቱ መድረክ  ባለሃብቶቹ "በገበታ ለሸገር" ፕሮጀክት የነበራቸውን ተሳትፎ "በገበታ ለሀገር" ፕሮጀክት እንዲደግሙት ታስቦ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡

በፕሮጀክቱ  በታቀፉት ሥፍራዎች ያሉትን  የኢንቨስትመንት አማራጮችን በሚመለከት ሃሳብ የሚያቀርቡበትን ዕድል ለመፍጠር  መሰናዳቱንም  ተናግረዋል፡፡

በአምራች ዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች  በፕሮጀክቱ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ ሥፍራዎችን ለባለሃብቶቹ በማስጎብኘት ተጨማሪ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያደርጋል ብለዋል፡፡

በአምራች ዘርፍ የተሰማሩ ውጭ ባለሃብቶችን ከአገር ውስጥ ባለሃብቶች ጋር በመጣመር በሆቴል፣ ቱሪዝምና በአገልግሎት ዘርፎች  ለማሰማራት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ኢትዮጵያ የምታከናውናቸውን የልማት ሥራዎች እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡

በፕሮጀክቱ በተያዙት ቦታዎች ያሉትን የኢንቨስትመንት አማራጮችን እንደሚያጤኗቸውም አስታውቀዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አነሳሽነት በጎርጎራ፣ በኮይሻና በወንጪ የሚካሄደው የ''ገበታ ለሀገር''  ፕሮጀክት ኢትዮጵውያንን፣ የውጭ ዜጎችን፣ የውጭ መንግሥታትንና የልማት አጋሮችን በማስተባበር በ3 ቢሊየን ብር እንደሚገነባ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም