ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የብር ኖቶች ለውጥ ማድረጓ ወቅታዊና አስፈላጊ ነው- አስተያየት ሰጪዎች

አዲስ አበባ መስከረም  26/2013 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያ የብር ኖቶች ለውጥ ማድረጓ ''ወቅታዊና አስፈላጊ'' ይሉታል ኢዜአ ማህበራዊ የትስስር ገጽ የዳሰሳ ጥናት ተሳታፊዎች።

ኢትዮጵያ ለ23 ዓመታት ያህል የተገለገለባቸውን ባለ10 ፣ባለ 50ና ባለ100 ብር ኖቶችን በያዝነው ወር መቀየር ጀምራለች።

በተጨማሪም አዲስ የባለ 200 ብር ኖት ሥራ ላይ አውላለች።

መንግሥት አዲሶቹ ኖቶች የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባትን ለማስተካከል፣ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርንና ሕገ ወጥ ንግድን ለማስቀረትና ሙስናንን ለመዋጋት እንደሚያስችሉ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ለአንድ ሳምንት በማህበራዊ የትስስር ገጹ ላይ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ተሳታፊዎች 95 በመቶ በላይ የሚሆኑት የኖቶቹ ለውጡን ''አስፈላጊ''ብሎም ''ወቅታዊ'' ነው ብለዋል።

ከተሳታፊዎቹ 54 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑት የኖቶቹ  ቅያሪ  ምጣኔ ሃብታዊና አገራዊ ጠቀሜታውን ''ከፍተኛ'' ያሉት ሲሆን፣ 41 በመቶ የሚሆኑት ''መካከለኛ'' በሚል ደረጃ ሰጥተውታል።።

ቀሪዎቹ  አስተያየት ሰጪዎች  የሰጡት ደረጃ ደግሞ ''መጠነኛ'' ብለው ነው።

አብዛኛዎቹ  የጥናቱ ተሳታፊዎች የኖቶቹ ለውጥ ምጣኔያዊና አገራዊ ጠቀሜታው እንዳለው በመግለጽ መንግሥትና የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የሚያነሱትን ሃሳብ ያጠናክራሉ።

በሌላ በኩል የብር ኖቶቹን ለውጥ ሂደት በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ በሚመለከታቸው አካላት ለህብረተሰቡ የሚሰጠው በቂና ወቅታዊ መረጃ ተጠይቀው 50 በመቶ የሚሆኑት ''በመጠኑ ግልጽ'' ብለውታል።

ከተሳታፊዎቹ 23 በመቶ የሚሆኑት ''ግልጽነት ይጎድለዋል'' ያሉ ሲሆን፣ 27 በመቶ የሚሆኑት የጥናቱ ተሳታፊዎች ደግሞ ''ግልጽ ነው'' እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና የሚመለከታቸው አካላት በኖቶቹ ለውጥ ላይ አርሶና አርብቶ አደሩን ጨምሮ ለህብረተሰቡ በቂና ወቅታዊ መረጃ በመስጠት ላይ ውስንነቶች እንደሚታይባቸው ተሳታፊዎቹ አመልክተዋል።

የባለ 200 ብር ኖት ወደ ገንዘብ ዝውውር ውስጥ መግባቱ ''የኢኮኖሚውን እንቅስቃሴ ያሳድገዋል'' የሚል ሃሳብ አስፍረዋል።

አብዛኛዎቹ የጥናቱ ተሳታፊዎች ከፍተኛ ዋጋ የለው የብር ኖት መዘጋጀቱ ሚናው ''የላቀ''መሆኑን ገልጸዋል።

''ብዙ የብር ኖቶች ከመሸከም ያድናል።የህትመት ወጪንም ይቀንሳል''ብለዋል በዳሰሳ ጥናቱ።

የጥናቱ ተሳታፊዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ መንግሥትና የጸጥታ አካላት የኖቶቹን ለውጥ በጥንቃቄ እንዲያስፈጽሙም አሳስበዋል።

በጥቂቶች እጅ የተከማቹት ኖቶች በአዲሶቹ የብር ኖቶች እንዳይለወጡ ክትትል እንዲደረግ  የሚያሳስቡ መልዕክቶችም  አስፍረዋል።

እንዲሁም  የባለ አንድ ሺህ ብር ኖት ቢታተም የሚል ሃሳብ አቅርበዋል።

በኖቶቹ ላይ የተካተቱት አዳዲስ ምስሎች ለአገር ገጽታ ግንባታ ያላቸውን ሚናም ''የላቀ''በማለት አስተያየት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም