ቀጥታ፡

በሀዋሳ ገጠር ቀበሌዎች የተገነቡ 23 የውሀ ቦኖዎች ለአገልግሎት በቁ

ሀዋሳ፣ መስከረም 26/2013 (ኢዜአ) በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ገጠር ቀበሌዎች ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ 23 የውሃ ቦኖዎች ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት በቁ፡፡

በሀዋሳ ሀዌላ ቱላ ክፍለ ከተማ አምስት የገጠር ቀበሌዎች ህብረተሰብ ተደራሽ ለማድረግ  የተገነቡት  የውሃ ማደያ ቦኖዎች የመረቁት የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ እንዳሉት መንግስት የነዋሪዎች የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡

የውሃ ማደያ ቦኖዎቹ ከ15  ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎባቸው በሶስት ወራት ውስጥ የተገነቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ በመገንባት  ለአገልግሎት እንዲበቁ የነዋሪዎችና መንግስት መናበብ ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው  አቶ ጥራቱ ተናግረዋል፡፡

የተጀመሩትንም ሆነ አዲስ የልማት ተግባራት ማቀድና ማጠናቀቅ እንደሚቻል አሁን ላይ ያለው የመንግስት አደረጃጀት በግልጽ እያሳየ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው የግል ጥቅማቸው የቀረባቸው አካላት እያደረጉት ካለው ሴራ ህዝቡ መጠንቀቅ እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

ነዋሪው ሠላሙን አጠናክሮ ወንድማማችነትን በማጎልበት ሃገራዊ አንድነትና ዘላቂ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ውሃና ፈሳሽ አገልግሎት ድርጅት ኃላፊ አቶ ዳዊት ለላሞ በበኩላቸው የውሃ ቦኖዎችን ለመገንባት ከ16 ኪሎ ሜትር በላይ የውሃ መስመር ዝርጋታ መከናወኑን ገልጸዋል።

የተገነቡት የውሃ ማደያ ቦኖዎች  ከ41 ሺህ 500 በላይ  ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ አመልክተው

በበጀት ዓመቱ ተጨማሪ የመጠጥ ውሀ ልማት ስራዎች ለማከናወን  ወደ ተግባር መግባቱንም ተናግረዋል፡፡

ጋራ ሊቀታ፣ ጨፋሲኔ፣ ገመጦ፣ ቱላና ሀሜሳ 23ቱ የውሃ ማደያ ቦኖዎች የተገነቡባቸው ቀበሌዎች  ናቸው፡፡

ከጨፋሲኔ ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል  ወይዘሮ ሳፋዬ ሳኩማ በሰጡት አስተያየት ንጹህ መጠጥ ውሃ ካለው የቦታ ርቀት የተነሳ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸው ሲያባክኑ እንደነበር  አስታውሰዋል።

በአቅራቢያቸው የተገነባው  የውሃ ማደያ ቦኖ  የነበረባቸውን ችግር እንደሚያቃልልላቸው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም