ቀጥታ፡

የአስተዳደሩ የጤና መሪ እቅድ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ የሚገኙ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ለመከላከል ትኩረት ሰጥቷል

ሃዋሳ መስከረም 26/2013 (ኢዜአ) የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የአስር ዓመቱ መሪ እቅድ በህብረተሰቡ ጤና ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ የሚገኙ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ይበለጥ ትኩረት መስጠቱ ተገለጸ።

የአስተዳደሩ  ጤና መምሪያ  ባለፉት አምስት ዓመታት ባከናወናቸው የጤና ሥራዎችና የቀጣይ አስር ዓመት መሪ እቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው።

የመምሪያው  ኃላፊው አቶ ሙንጣሻ ብርሀኑ በምክክር መድረኩ እንደገለፁት ባለፉት አምስት ዓመታት በከተማዋ የጤና አገልግሎትን ጥራትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ  የሚያግዙ ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል።

በተለይ በሽታን መከላከል ላይ ያተኮረ የጤና አገልግሎት ከመስጠት አኳያ ህብረተሰቡን ከበሽታ ለመጠበቅ በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አማካይነት በተከናወኑት ሥራዎች በርካታ ሞዴል ቤተሰቦችን ማፍራት መቻሉን ጠቅሰዋል።

ሆኖም በሙሉ አቅም ያልተተገበሩ ሥራዎች መኖራቸውን የተናገሩት ኃላፊው በቀጣይ አስር ዓመታት ትኩረት የሚሰጧቸው በርካታ የጤና አገልግሎት ሥራዎች እንዳሉ አስረድተዋል።

ከነዚህም በተለይ  ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከል ዋንኛዎቹ እንደሆኑ አመልክተው የእናቶችና ጨቅላ ሕፃናትን ሞት መቀነስ እንዲሁም በዘርፉ በሁሉም አገልግሎቶች ላይ በቂ የሰው ኃይል ማፍራት ሌላኛው መሆኑን ጠቅሰዋል።

የህብረተሰቡ የአኗኗር ዘይቤ እየተቀየረ ከመምጣቱ  ጋር ተያይዞ በሀዋሳ ደም ግፊት ፣ ስኳር ፣ የማህፀን ጫፍ ካንሰርና መሰል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ተጋላጭነት በሰፊው እንደሚስተዋል ተናግረዋል።

በመሪ እቅዱ  ይበልጥ  ትኩረት ሰጥተን ከምሰራቸው ሥራዎች መካከል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከል ነው ያሉት የመምሪያው ኃላፊው መንስኤዎችን በጥናት በመለየት ህብረተሰቡ ራሱን ከነዚህ በሽታዎች እንዲጠብቅ የማስገንዘብና የማንቃት ሥራ እንደሚከናወን አስረድተዋል።

ለነዚህ በሽታዎች ህሙማን የተሟላ የህክምና አገልግሎቶችን ለመስጠት  የጤና ተቋማትን ደረጃ የማሻሻልና በመሳሪያ የማሟላት ስራ ይካሄዳል።

በከተማዋ ቀደም ሲል የነበረውና አሁን የቀነሰው የብስክሌት ትራንስፖርት የመጠቀም ልምድ ለማዳበር እና  በግል ስፖርት የሚያሰሩ ሰዎችን በተደራጀ መልኩ በማስተሳሰር የማስ ስፖርትን በተቀናጀ መልኩ ለማስፋፋትም በመሪ ዕቅድ ተካቷል።

በተለይ ለበሽታ የሚያጋልጡ የቅባት ነክ ምግቦች አጠቃቀምን ለማስተካከል ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በቀጣይ እንደሚከናወኑ ተመልክቷል።

ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው የምክክር መድረኩ የአስተዳደር አካላት ፣ የጤና ዘርፍ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ  ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም