አምቦ እና አክሱም ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት ለማስጀመር መዘጋጀታቸውን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
አምቦ እና አክሱም ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት ለማስጀመር መዘጋጀታቸውን ገለጹ
አምቦ፣አክሱም፣መስከረም 26/2013 (ኢዜአ) አምቦ እና አክሱም ዩኒቨርሲቲዎች በወረርሽኙ ምክንያት ተቋርጦ የቆየውን የመማር ማስተማር ስራ ለመጀመር መዘጋጀታቸውን ገለጹ፡፡
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ህዝብ ግንኙነት ዳይረክተር ዶክተር መንግስቱ ቱሉ እንዳሉት ተቋሙ ከሳይንስናከፍተኛ ትምህርትተቋማት ሚኒስቴር በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ለመልሶ ቅበላው ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡
በትምህርት ዘመኑ የመማር ማስተማር ስራ የሚጀመረው ኮሮናን ለመከላከል የሚያስችሉ ጥንቃቄዎችን በማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ለዚሁ ተግባር ባቋቋመው ኮሚቴ አማካይነት ቫይረሱን እየተከላከሉ የመማር ማስተማሩን ሂደት ለማስቀጠል የሚያስችሉ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በአንድ የተማሪዎች መኝታ ክፍል ውስጥ ስምንት ተማሪዎች ይመደቡ የነበረው አሁን ወደ አራት ዝቅ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ከንኪኪ ነጻ የሆኑ መታጠቢያዎች በአራቱም የዩኒቨርሲቲው ካምፓሶቹ መዘጋጀታቸው አመልክተው ጨንብልና የንጽህና መጠበቂያ ግብዓቶች መሟላታቸውን ገልጸዋል፡፡
የመማር ማስተማር ስራው ሲጀመር ለአንድ ተማሪ ሁለት ከጨርቅ የተሰሩ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችና በዩኒቨርሲቲው የተሰራ ሳኒታይዘር መዘጋጀቱንም ዶክተር መንግስቱ አብራርተዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የሬጂስትራር ጽህፈት ቤት ዳይረክተር አቶ ማንደፍሮ ለገሰ በበኩላቸው የተቋሙ ቅድመ ዝግጅት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር ገምጋሚ ቡድኑ ካረጋገጠ በኋላ የመማር ማስተማሩ ስራ እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው 4 ሺህ 439 ተመራቂ ተማሪዎችን በመጀመሪያው ዙር እንደሚቀበል አመልክተው ቀሪዎቹን ተማሪዎች ሚኒስቴሩ በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሰረት እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
የአምቦ ከተማ ነዋሪው የአንደኛ ዓመት የአፋን ኦሮሞ ተማሪ ሲፈን ተስፋዬ በሰጠችው አስተያየት"መደበኛ ትምህርት ይጀመራል መባሉን ስሰማ በጣም ተደስቻለሁ፤ ከጤና ባለሙዎችየሚሰጠውየጤናአጠባበቅ መመሪያ ተግባራዊ አድርጌትምህርቱን ለመከታተልም ዝግጁ ነኝ" ብላለች፡፡
ከኮሮና ጥንቃቄ ባሻገር ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲመጡ ከትምህርት ውጪ ፖለቲካዊና ኃይማኖታዊ አጀንዳ ይዘው መሆን እንደሌለባቸው አስተያየቱን የሰጠው ደግሞ የሁለተኛ ዓመት የኬሚስትሪ ተማሪ አብረሃም ምትኩ ነው፡፡
አምቦ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም የሚያስተምራቸው ከ25 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንዳሉት ተመልክቷል።
በሌላ በኩል የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ለማሰጀመር የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማከናወኑን በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር የተቋቋመ ግብረ ኃይል ገለጸ።
በግብረ ኃይሉ በትግራይ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የሱፐር ቪዥን ቡድን መሪ ዶክተር ዘለአለም አሰፋ ለኢዜአ እንደተናገሩት አክሱም ዩኒቨርሲቲ መሰረታዊ የመገምገሚያ መስፈርቶች በማሟላት ትምህርት ለመጀመር መዘጋጀቱን በመስክ ምልከታ አረጋግጠዋል።
በሽታው ለመከላከል የመመገቢያ፣መማሪያ እና ሌሎች ተማሪዎች የሚገለገሉባቸው ክፍሎች የኬሚካል ርጭት ተደርጎላቸው ለአገልግሎት ዝርጁ መሆናችውን ማረጋገጥ መቻሉን ተናገረዋል።
ለለይቆ ማቆያነት ሲያገለግል የቆየው የሽረ ካምፓስ ያልተሟሉ ስራዎች እንደሚቀሩ እንዲሁም በአገልገሎት መስጫ ቦታዎች ከእጅ ንክኪ ነጻ የሆነ የመታጠቢያ ሟሟላት ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ማንኛውም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን መቀበል የሚያስችል ሁኔታ ላይ መሆኑን አለመሆኑን የሚታወቀው በመስክ ግምገማው በተጠናቀቀው መረጃ መሰረት ውጤቱ በሚኒስቴሩ ይገለፃል ብለዋል።
የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ገብረእየሱስ ብርሃነ በበኩላቸው ሁሉም ክፍሎች እና መገልገያ ንብረቶች ታድሰዋል፣የሁሉም ትምህርት ክፍል ኃላፊዎች እና መምህራን ለትምህርት ተዘጋጅተዋል ብለዋል።
ከእጅ ንክኪ ነጻ የሆነ የእጅ መታጠቢያ በመግቢያ እና መውጫ በር እንዲሁም ተማሪዎች በሚገለገሉባቸው ስፍራዎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሰቀቁሶች ለማሟላት በግዥ ሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመው በሽረ ካምፓስ የቀሩ ስራዎች በዚህ ሳምንት ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ እንደሚሆን ገልጸዋል።
የኮሮና መከላከልና ሰላማዊ የመማር ማሰተማር ስራ የሚያስተባብር ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ከባለደርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኢያሱ ተስፋይ ተቋሙ አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርግና የወጡ መመሪያዎችን እንዲተገብር ቦርዱ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ተናግረዋል።
ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራን ለማስቀጠል እና ቫይረሱን ለመከላከል የሰራ ክፍፍል አድርገን እንሰራለን ብለዋል።