ቀጥታ፡

ደቡብ ምዕራብ 11ኛ የኢትዮጵያ ክልል እንዲሆን ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅ ተወሰነ

አዲስ አበባ መስከረም  26/2013 ( ኢዜአ) የደቡብ ምዕራብ ህዝቦች 11ኛ የኢትዮጵያ ክልል መሆን እንዲችሉ በምርጫ ቦርድ አስፈጻሚነት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ወሰነ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በ6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባኤው በአጀንዳነት ከተመለከታቸው አበይት ጉዳዮች መካከል አንዱ የደቡብ ምዕራብ ክልል ጉዳይ ነው።

የምክር ቤቱ የሕገ መንግስት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ ሕዝቦች ያቀረቡትን ክልል የመሆን ጥያቄ አብራርቷል።

የኮሚቴው ጸሓፊ አቶ ወርቁ አዳሙ እንዳሉት የከፋ፣ የቤንች ሸኮ፣ የምዕራብ ኦሞ፣ ዳውሮና ሸካ ዞኖች እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳ በጋራ ክልል ለመመስረት መወሰናቸውን ለምክር ቤቱ አሳውቀዋል።

የዞኖቹ ምክር ቤቶችና ልዩ ወረዳው አስፋለጊውን መስፈርት አሟልተው መቅረባቸውን የገለጹት አቶ ወርቁ አራቱ ዞኖችና ልዩ ወረዳው ውሳኔውን በሙሉ ድምጽ ያጸደቁ ሲሆን አንዱ ዞን በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል ብለዋል።

ዞኖቹ ከኢህአዴግ መንግስት በፊት በአንድ ጠቅላይ ግዛት ስር የነበሩና ተቀራራቢ ቋንቋ፣ ባህልና መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እንደሚጋሩም ገልጸዋል ነው ያሉት።

ቋሚ ኮሚቴው በሕገ መንግስቱ መሰረት ክልል የመሆን ጥያቄው መቅረቡን ካረጋገጠ በኋላ በዛሬው እለት በምርጫ ቦርድ አስፈጻሚነት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅ የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ አባላት አቅርበዋል።

የውሳኔ ሀሳቡ ለምክር ቤቱ አባላት ከቀረበ በኋላ አባላቱ ቀድሞ ክልል ለመሆን የጠየቁት ዞኖች ጉዳያቸው የት ደረሰ ከሚል ጀምሮ የተለያዩ ሃሳቦችን አንጸባርቀዋል።

በተጨማሪም በዚህ ዓመት ምርጫ ቦርድ ስድስትኛውን አገር አቀፍ ምርጫ የሚያካሄድ እንደመሆኑ የስራ ጫና ሊያገጥም እንደሚችል ስጋትም አቅርበዋል።

የዞኖች አካሄድ ለሌሎችም ምሳሌ የሚሆንና ሂደቱም የሚደገፍ መሆኑን ነው የገለጹት።

የምክር ቤቱ የሕገ መንግስት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮችና ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሎሚ በዶ በደቡብ ክለል አጠቃላይ 13 የዞን ምክር ቤቶች ክልል የመሆን ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

በዚህ ዓመት ኮቪድ 19 ወረርሺኝን ጨምሮ ሌሎች ተደራራቢ አገራዊ ጉዳዮች በማጋጠማቸው ምክንያት እንጂ የሌሎቹ ጉዳይ አያስፈልግም ወይም ተዘንግቷል ማለት አይደለም ብለዋል።

ለክልልነት ጥያቄ አስፈላጊውን ሂደት ጨርሶና አስፈላጊውን መስፈር አሟልቶ የመጣ ከሆነ ወደ ውሳኔ ይደረሳልም በማለት አስረድተዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤው አቶ አደም ፋራህ በበኩላቸው በምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔውን ማካሄድ እንዲችል የፌዴሬሽን ምክር ቤት በቅርበት ያግዛል ብለዋል።

ሕዝበ ውሳኔው ከተቻለ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ፈጥኖ የሚካሄድበት መንገድም ሊመቻች እንደሚችል ገልጸዋል። 

ባለፈው ዓመት 10ኛ ክልል የሆነው ሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ተካሄዶ ክልልነቱን ማረጋገጡ ይታወቃል።

ምክር ቤቱ የሕገ መንግስት ትርጉም የሚያስፈልጋቸውና የማያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን በሌሎች አጀንዳዎችም ላይ ውይይት አድርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም