ኢትዮጵያና ኤርትራ የጀመሩት ግንኙነት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ

86
ጎባ ጅማ  ነገሌ አምቦ ነቀምቴ ጊምቢ አምሌ 7/2010 ኢትዮጵያና ኤርትራ የጀመሩት ግንኙነት ዘላቂ ሰላምንና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ  ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር በጎባ ፣ጅማ ፣ነገሌ ፣አምቦ እና ነቀምቴ ከተሞች አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ፡፡ ከጎባ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ሰይፉ ኡስማኤል ለኢዜአ እንዳሉት ሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች ለ20 ዓመታት ተለያይተው መቆየታቸው  ተጎድተዋል፡፡ "አሁን በተፈጠረው ሰላማዊ ግንኙነት የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች በኢኮኖሚና በሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ለማስተሳሰር ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል" ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ  ያደረጉት አቀባበል የሀገራቱ ዜጎች ለኤርትራዊያን ወንድሞቻቸው ያላቸውን ፍቅርና ለሰላም ቁርጠኝነታቸውን በተግባር ያሳዩበት አጋጣሚ መሆኑን የተናገረው ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ነስሩዲን አብዱልጀዋድ ናቸው፡፡ የጎባ ሁለተኛ ደረጃ መምህር የሆኑት አቶ ብርሃኑ ከተማ  በበኩላቸው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መመለሱ  ዘላቂ ሰላምንና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ  ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡ " ጉብኝቱ ከሁለቱ ሀገራትም ባለፈ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰላም የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል"ብለዋል፡፡ አቶ ብርሃኑ ህዝቡ በሀገሪቱ አሁን የተጀመሩ ሁለንተናዊ ለውጦች ከግብ እንዲደርሱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጎን እንድቆም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከጅማ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ከኤርትራዊ አባት የሚወለዱት አቶ ስምኦን  አስገድ በሰጡት አስተያየት በኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም እንዲወርድ ለዘመናት ይመኙ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ አሁን የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም አባቱንና ዘመዶቼን ለማየት ፍላጎታቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ሌላው የከተማው ጅሬን ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጃፈር ሁሴን  በበኩላቸው አሁን የተጀመረውን ሰላም ዘላቂ እንዲሆን የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግስታት ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ለጋራ ተጠቃሚነት መስራት እንዳለባቸው ያመለከቱት በከተማዋ የቆጪ ሰፈር ነዋሪ ወይዘሮ እናትነሽ ወርቁ  ለኤርትራ ፕሬዘዳት የተደረገው አቀባበል እንዳስደሰታቸውም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ በጉጂ ዞን ነገሌ ከተማ የቀበሌ ሶስት ነዋሪ አቶ ግደይ ሀጎስ በሰጡት አስተያየት አሸናፊና ተሸናፊ ያልታየበት የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ከመለያየት በስተቀር ውጤት አልባ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የወሰዱት የሰላም እርምጃ የሚደገፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦችና መንግስታት በትብብርና በጋራ ከሰሩ በቂ የተፈጥሮ ሀብት ያላቸው በመሆኑ ለተቀረው አለም እንደሚተርፉም ጠቁመዋል፡፡ የከተማው ቀበሌ አንድ  ነዋሪ ቄስ መለሰ ነጋ  " የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላምና ፍቅር ፈላጊ መሆኑን አቶ ኢሳያስ አፈወርቂን ለመቀበል አደባባይ በመውጣት በተግባር አሳይቷል" ብለዋል፡፡ አቀባበሉ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦችና መሪዎች አለም አቀፋዊ የሰላም እውቅና ያገኙበት የጋራ ወዳጅነት የተረጋገጠበት መጥፎ ታሪክ የተሰበረበትና የተቀየረበት እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ አቶ ብርሀኑ በቀለ የተባሉት ነዋሪ በበኩላቸው " ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአስመራ ከተማ በኤርትራዊ ወገኖቻችን የተደረገው አቀባበል በአዲስ አበባ ከተማ መደገሙ የሚያኮራ ነው "ብለዋል፡፡ ለዓመታት ተለያየተው የኖሩ ወንድማማች ህዝቦች እንዲገናኙ ላደረጉት ለሁለቱም ሀገራት መሪዎች ምስጋና እንደሚገባቸውም አመልከተዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከአምቦ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ጌታቸው አንበሳ እንዳሉት የኤርትራው ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው የሀገራቱን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያጠናክራል፡፡ የሁለቱ ሀገራት ሰላም ማውረድም ከህብረተሰቡ ማህበራዊ ግንኙነት በላይ የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ነገራ ፈይሳ በፕሬዘዳንቱ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው  መደሰታቸውን አመልክተው ተለያይተው የነበሩት የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች መገናኘታቸው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡ " ኢትዮጵያ  ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከሯ በሁሉም ዘርፍ ለህዝቦቿ ተጠቃሚነት የሰጠችውን ታላቅ ቦታ ያሳያል " ያሉት ደግሞ ሌላው የአምቦ ከተማ ነዋሪ አቶ ወርቅነህ አሳምነው ናቸው፡፡ በሁለቱ ሀገራት መካከል አሀን የተጀመረው ግንኙነት ለህዝቦቻቸው የጋራ ተጠቃሚነት የሚያጠናክርና በቀጠናው ተቀዛቅዞ የነበረው የኢኮኖሚ ሁኔታም እንደገና ማንሰራራት እንደሚችልም አመልክተዋል፡፡ በሌላ በኩል በነቀምቴ ከተማ ቀበሌ ሶስት ነዋሪዎች መካከል  አቶ ኤቢሣ ጉያሣ በሰጡት አስተያየት ሻክሮ የቆየው የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት በሰላምና በፍቅር እንደገና መመለስ የተቻለው  በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥረት መሆኑ ተናግረዋል፡፡ በከተማው የሚኖሩት የህግ ባለሙያ አቶ ደረጀ አበበ በበኩላቸው  በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው ቅራኔ በሰላማዊ መንገድ መቋጨቱ በፖለቲካ፣ኢኮኖሚና ማህበራዊ መስኮች ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል፡፡ "በሁለቱ ሀገራት  መካከል ሠላም ወረደ ማለት ለምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ሠላም ዋስትና ነው "ያሉት ደግሞ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የሆኑት አቶ አሰፋ ገርቢ ናቸው። መቀራረቡ የተራራቁ ቤተሰቦችን ከማገናኘት ባለፈ ለኢኮኖሚ ዕድገታቸው የጎላ ጠቀሜታ አንዳለው አመለክተዋል፡፡ የከተማው የሀገር ሽማግሌ አቶ ተሾመ ገመዳ በበኩላቸው "ዶክተር አቢይ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድ መድኃኒት ናቸው" ብለዋል። በተመሳሳይ የጊምቢ ከተማ ነዋሪው አቶ ሃይሌ ሪቂቱ በሰጡት አስተያት ሁለቱ ሀገራት ለረዥም ዓመታት በጦርነት ምክንያት ተራርቀውና ተለያይተው ቢቆዩም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥረት መቀራረብ እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡ የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያን ለመጎበኘት መምጣታቸው መደሰታቸውን ጠቅሰው የሁለቱ ሀገራት መቀራረብ የጋራ ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያጠናክረው አመልክተዋል፡፡ ሌላው አስተያየት ሰጪ ወጣት ማሙሽ ነገደ በበኩሉ  ሁለቱ ሀገራት ተራርቀው ቢቆዩም ቀደም ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትር  ዶክተር አብይ አህመድ  ኤርትራ አሁን ደግሞ  ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ግንኙነታቸው ታድሶ የአብሮ  የመኖር እድል  እንደሚኖራቸው ብሎ እንደሚያምን  ገልጿል። ሁለቱ ሀገራት ለዘመናት ያቆራረጣቸውን ቁርሾ ረስተው በይቅርታና በፍቅር  አብረው ለመጓዝ መወሰናቸው ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው የተናገሩት ደግሞ  ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ዳንኤል  ሞገስ ናቸው። አቶ ዳንኤል "አሁን በሀገራችንና  ኤርትራ መካከል  የሚነፍሰውን የሰላምና የመተባበር ስሜት እኛም ባለንበት  ሰላማችንን በማስጠበቅ የተጀመረውን የመደመር ጉዞ ለማሳካት መረባረብ ይኖርብናል" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም