ቀጥታ፡

በመዲናዋ በ2013 በጀት አመት 525 ኪሎ ሜትር የጥገና ስራ ይከናወናል---የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26/2013(ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በ2013 በጀት አመት በመዲናው በተለያዩ አካባቢዎች 525 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍኑ መንገዶች ጥገና ስራ ለማከናወን እቅድ መያዙን አስታወቋል፡፡

ባለስልጣኑ የአዲስ አበባን የመንገድ መሰረተ ልማት ለማሟላትና ተደራሽነቱን ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ የመንገድ ግንባታና ጥገና ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን አመልክቷል፡፡

መስራቤቱ እንደገለጸው በበጀት አመቱ 525 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የአስፋልት፣ ድልድይ፣ ድሬኔጅ ፣ የአክሰስ መንገድ እና ሌሎች በርካታ ልዩ ልዩ የጥገና ስራዎች የሚከናወኑ ናቸው።

በዚህም 130 ኪ.ሜ የአስፋልት መንገድ ጥገና፣ 68 ኪ.ሜ የጠጠር መንገድ ጥገና፣ 50 ኪ.ሜ የኮብል ስቶን መንገድ ጥገና፣ 20 ኪ.ሜ የእግረኛ መንድና ከርቭ ስቶን ጥገና፣ 257 ኪ.ሜ የድሬኔጅ መስመር ጥገናና የፉካና ቦይ ጠረጋ ስራዎች ሲሆኑ የማንሆል ክዳን እንዲሁም የድጋፍ ግንብና የድልድይ ጥገና ስራዎች የሚከናወን ይሆናል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች መደበኛና ወቅታዊ ተደራሽ ጥገና ማድረግ፣ በነባር መንገዶች የከርቭስቶን ግንባታ ማከናወን፣ የመንገድ ዳር መብራት ጥገና ስራዎችን ማከናወንና ሌሎች ጥገና የሚያስፈልጋቸው ስራዎችን በራስ ኃይል ለማከናወን እቅድ እንዳለው ጠቅሷል፡፡

የጥገና ስራው የሚከናወነው በከተማው በተለያዩ አካባቢዎች የትራፊክ እንቅስቃሴን የሚያስተጓጉሉና ለእግረኛ እንቅስቃሴ አስቸጋሪ በሆኑ ቦታዎች ላይ መሆኑን ነ ባለስጣኑ የገለጻው፡፡

ባለስልጣኑ በ2012 በጀት አመት 544 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ልዩ ልዩ የጥገና ስራዎችን ማከናወኑ ይታወቃል፡፡

በዚህም በ2013 በጀት አመት በከተማችን በተለያዩ ምክንያት እየተበላሹ እና ቅሬታን የሚያስነሱ አካባቢዎችን የመልሶ ግንባታና ጥገና ስራዎችን በስፋት በማናከወን የህብረተሰቡን የመንገድ ጥያቄዎች ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ ከመስራቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም