የወርቅ ግዥ መመርያ ላይ ማሻሻያ በመደረጉ የወጪ ንግዱ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል - ኢዜአ አማርኛ
የወርቅ ግዥ መመርያ ላይ ማሻሻያ በመደረጉ የወጪ ንግዱ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል
አዲስ አበባ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ህገ ወጥ የወርቅ ዝውውርን ለመግታት የወርቅ ግዥ መመርያ ላይ ማሻሻያ በማድረጉ የወጪ ንግዱ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ብሉምበረግ ዘገበ፡፡
የመንግስት ጥረት በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሃብቶችን ለመሳብም ያለመ ነው ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ የወርቅ ኢንዱስትሪ በአብዛኛው በአነስተኛ አምራቾች ላይ የተንጠለጠለ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ይህ አንዳለ ሆኖ "ኒውሞንት ኮርፖሬሽን" እና የአወስትራሊያው "አላይድ የወርቅ ኮርፖሬሸን" በአገሪቱ ወርቅ ፍለጋ ላይ መሰማራታቸው ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት መደበኛ ያልሆነውን የግብይት ሰንሰለት በመበጠስ ዝውውሩ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኩል እንዲከናወን ማድረጉ አገሪቱ በኢንቨስተሮች ተመራጭ እንድትሆን ማድረጉን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
“ጥድፊያው የጅማሮው ማሳያ ነው” ሲሉ በለንደን የተመዘገበውና በወርቅና መዳብ ፍለጋ ላይ የተሰማራው የከፊ ማይንራል የግል ኩባንያ ዋና ሊቀመንበር ሀሪ አናኖስታራስ ተናግረዋል፡፡
ከፊ ማይንራል ኩባንያ በምዕራብ ኢትዮጵያ በቱሉ ካፒ አካባቢ በወርቅ ማዕድን ፍለጋ ላይ መሰማራቱ ይታወቃል፡፡
“ሰዎች ወደዚህ መምጣት ጀምረዋል፣ የዚህ ምክንያት ደግሞ መንግስት ስር ነቀል በሆነ መልኩ አሰራሩን መቀየር መጀመሩ ነው፤ መንግስት ነገሮችን በጥርጣሬ ከመመልከት ወጥቶ ለሁሉም በሩን ከፍቶ መቀበልና ቅሬታዎችን ማዳመጥ ጀምሯል ” ብሏል ዘገባው፡፡
እንደዘገባው ከሆነ ባለፈው ሐምሌና ነሐሴ ወራት ወደ ወጭ የተላከው ወርቅ 700 ኪሎ ግራም ሲሆን ምጣኔው ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በአራት እጥፍ የሚበልጥ ነው፡፡
ለወጪ ንግዱ ማደግ ምክንያት ነው የተባለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንከ ካለፈው ሰኔ መጀመሪያ አንስቶ የወርቅ ግብይት ዋጋውን ማሳደጉ ነው፡፡
አፍሪካውያን ወርቅ ላኪ አገራት በተያዘው ዓመት ከወርቅ ማዕድን የሚያገኙት ገቢ እንደሚጨምርም ብሉምበርግ በዘገባው ጠቁሟል፡፡.
የኢትዮጵያ አያያዝ የባለሃብቶችን ፍላጎት በእጅጉ እንዳነሳሳው ከኮፊ ማይንራል በተጨማሪ በእንግሊዝ 25 አባል ኢንዱስትሪዎችን የያዘው ማህበር ሊቀመንበር የሆኑት ሀሪ አናኖስታራስ ጨምረው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ከወራት በፊት እንደገለጹት ለባንኩ የሚቀርበው ወርቅ በከፍተኛ ደረጃ አሽቆልቁሎ የነበረ ሲሆን ከጥቂት ወራት ወዲህ መጠኑ እየጨመረ መጥታል።
ለዚህም የፖሊሲ ለውጡ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸው፣ ባለፈው ሐምሌ ወር ብቻ ከ72 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ የሚያወጣ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ መቅረቡን አመልክተዋል፡፡
ባንኩ በሚከተለው የወርቅ ግዥ መመርያ ላይ ማሻሻያ ከተደረገ ወዲህ በወር በአማካይ ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያለው ወርቅ መቅረብ እንደጀመረ መገለጹ ይታወሳል፡፡
የዋጋ ማሻሻያ በማድረግ የግዥ ሥርዓት የሚፈጸምበት መመርያ ከወጣ በኋላ በየወሩ የሚገኘው ገቢ ከ30 ሚሊዮን ዶላር ጀምሮ ወደ 50 ሚሊዮን ዶላር በኋላም ወደ 60 ሚሊዮን ዶላር ማደጉንና በሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም የነበረው የወርቅ ንግድ ገቢ ወደ 72 ሚሊዮን ዶላር ማሻቀቡን ዶክተር ይናገር አመልክቷል።
በአወስትራሊያ የተመዘገበው "መጋዶ የወርቅ ኩባንያ" በደቡብና ምዕራብ ኢትዮጵያ አምስት የወርቅ ፍለጋ ቦታዎች ላይ እየሰራ ሲሆን የካናዳው "ሰን ፒክ ብረታ ብረት ኮርፖሬሽን" ደግሞ በሰሜን ኢትዮጵያ በወርቅ ፍለጋ ላይ ለመሰማራት መዘጋጀቱን ብሉምበረግ ጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት የማዕድን ዘርፉ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ 10 በመቶ ለማድረስ አልሞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡