ጎንደር እና ደባርቅ ዩኒቨርሲቲዎች የቅድመ ቅበላ ዝግጅታቸው ትምህርት ለማስጀመር እንደሚያስችላቸው ገለጹ

ጎንደር፣መስከረም 26/2013 (ኢዜአ) ጎንደር እና ደባርቅ ዩኒቨርሲቲዎች የቅድመ ተማሪዎች ቅበላ ዝግጅት ትምህርት ለመጀመር እንደሚያስችላቸው ማረጋገጡን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር ገምጋሚ ቡድን ገለጸ፡፡

ገምጋሚ ቡድኑ በዩኒቨርሲቲዎቹ  የመስክ ምልከታ በማድረግ ከተቋማቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር  የጋራ ውይይት አካሄዷል።

በሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት ብቃትና ምዘና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይግዛው በዚህ ወቅት እንዳሉት የ2013 ዓ.ም ትምህርት ለማስጀመር 11 ገምጋሚ ቡድኖች የዩኒቨርሲቲዎችን የቅድመ ዝግጅት በመገምገም ላይ ናቸው።

ኮሮናን  እየተከላከሉ የመማር ማስተማር ስራውን ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ጎንደርና ደባርቅ  ዩኒቨርሲቲዎች ያደረጉትን ቅድመ የተማሪዎች ቅበላ ዝግጅት መመልከታቸውን አስረድተዋል።

ሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች በተማሪዎች ማደሪያ፣ መማሪያ ክፍሎች፣ በመመገቢያ አዳራሾች፣ ቤተ-መጻህፍትና ሌሎች የአገልግሎት መስጫዎች ያለውን ዝግጁነት መልካም መሆኑን ቡድኑ  ገምግሟል ብለዋል፡፡

በተለይም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ስራውን ለማስጀመር ያደረጋቸው ቅድመ ዝግጅቶች በመልካም ተሞክሮነት የሚወሰዱ በመሆናቸው ቡድኑ ይህን ተሞክሮ ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚያስተላለፍ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን በበኩላቸው ተቋሙ የኮሮና ህሙማን ማገገሚያና ማቆያነት ሲያገለግሉ የቆዩ ህንጻዎች ለመማር ማስተማር ስራው እንዲወሉ ማዘጋጀቱን  አስረድተዋል፡፡

በተማሪዎች መመሪያ ፣ማደሪያና መመገቢያ አዳራሾችም ከእጅ ንክኪ ነጻ የእጅ ማስታጠቢያ ቴክኖሎጂዎች በበቂ ሁኔታ መደራጀታቸውን ጠቁመው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች በአስገዳጅነት ተግባራዊ ይደረጋሉ ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን በሶስት ዙር እንደሚቀበል ጠቁመው በመጀመሪው ዙር  5ሺ መደበኛ ተመራቂ ተማሪዎችን በመቀበል የጀመሩትን ትምህርት እንዲያጠናቅቁ የሚደረግ መሆኑን ዶክተር አስራት ተናግረዋል።

የተቋሙን ሰላምና ደህንነት ለማረጋጋጥም ከጸጥታ መዋቅር፣ ህብረተሰቡና ከተማ አስተዳዳሩ የተውጣጣ ግብረ ኃይል በማቋቋም ተማሪዎች በተረጋጋ መንፈስ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ይደረጋል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው የውሃና መብራት አገልግሎቶችን በተሟላ መንገድ እንዲገኝ አስፈላጊውን ጥረት ያደርጋል ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ማስተዋል ስዩም ናቸው።

ባለፈው ዓመት በኮሮና ምክንያት የተቋረጠውን "የጎንደር ቤተሰብ ፕሮጀክት" ዩኒቨርሲቲውንና የከተማውን ማህበረሰብ የሚያስተሳስር በመሆኑ ዘንድሮም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚደረግ መሆኑን አስታውቀዋል።  

የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር ጀጃው ደማሙ  ኮሮናን ለመከላከል የወጣውን ሀገር አቀፍ የጤና መመሪያ መሰረት በማድረግ በአንድ የመማሪያ ክፍል 25 ተማሪዎችን ለማስተማር ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

ገምጋሚ ቡድኑ  የባህርዳርና ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲዎችን  ቅድመ ዝግጅት  እንደሚገመግምም ተመልክቷል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም