የመረጠን ሕዝብ ውክልናውን እስከሚያነሳ ድረስ ሃላፊነታችንን መወጣታችንን እንቀጥላለን- የምክር ቤት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
የመረጠን ሕዝብ ውክልናውን እስከሚያነሳ ድረስ ሃላፊነታችንን መወጣታችንን እንቀጥላለን- የምክር ቤት አባላት
አዲስ አበባ መስከረም 26/2013 ( ኢዜአ) የመረጣቸው ሕዝብ ውክልናውን እስከሚያነሳ ድረስ የተቀበሉትን ህዝባዊ ሃላፊነት መወጣታቸውን እንደሚቀጥሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ የጋራ ስብሰባ የመክፈቻ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
የኮሮናወረርሽኝ የጥንቃቄ መንገዶችን በመተግበር ምርጫ እስከሚካሄድና የመረጣቸው ሕዝብ ውክልናውን እስከሚያነሳ ድረስ የተቀበሉትን አደራ መወጣታቸውን እንደሚቀጥሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የምክር ቤት አባላት ገልጸዋል።
ከመስከረም 25 በኋላ የምክር ቤቱ ህጋዊነት ላይ በአንዳንድ አካላት የሚነሱ ሃሳቦች የሕገ መንግስት መሰረት የሌላቸው መሆኑንም የምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል።
የምክር ቤት አባላትን ሕዝብ አምኖ የመረጣቸውና የበርካቶችን ውክልና የያዙ በመሆናቸው ሕዝብ ውክልናውን እስከሚያነሳ ድረስ ማገልገላችንን እንቀጥላለን ብለዋል።
በመሆኑም መንግሥት ያወጣቸውን አሰራሮች ተግባራዊነት በመከታተል አስፈጻሚውን አካል የመቆጣጠርና የመከታተል ሥራችንን እንቀጥላለን ነው ያሉት።
በምክር ቤቱ የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ፤ 6ኛው ብሄራዊ ምርጫ ቀደም ሲል ሊካሄድ ወጥቶ የነበረው መርሃ ገብር በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት መራዘሙን አስታውሰዋል።
ምክር ቤቱ የሕዝብን ደህንነት በማስቀደም ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ደረጃ በደረጃ ተከትሎ ምርጫውን ማራዘሙንም አብራርተዋል።
የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ያሳለፉትን ውሳኔ መተግር የአስፈጻሚ አካልና የሁሉም ክልሎች ግዴታ መሆን እንዳለበትም በግልጽ ይታወቃል ነው ያሉት።
በመሆኑም የአገሪቱን ህገ-መንግስት በመጻረር የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የተወከሉበትን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ በመጣስ የተካሄደ ምርጫ ህገ ወጥ መሆኑን ገለጸዋል።
ምክር ቤቱ የጤና ሚኒስቴር ባቀረበው ምክረ ሃሳብ መሰረት በ2013 ዓ.ም ምርጫው እንዲካሄድ ሲወስንም የህዝብን ጤና አደጋ ላይ ሊጥሉ የማይችሉ ሁኔታዎች መኖራቸውን ከመረመረ በኋላ መሆኑን አስንተዋል።
በምክር ቤቱ የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንዳሉትም መንግስት እያከናወነ ያለውን የምጣኔ ሃብት፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ የለውጥ ተግባር በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል።
የህዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች በህገ መንግስቱ መሰረት መንግስት የሚያወጣቸውን እቅዶች ተፈጻሚነት ክትትልና ድጋፍ ይቀጥላሉ።
ከመስከረም 25 በኋላ ህጋዊ መንግስት የለም በሚል አንዳንዶች ለሚያናፍሱት ወሬ ህዝቡ ሊደናገር እንደማይገባው ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ወቅት በማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብትና ፖለቲካ ዘርፍ ትኩረት በሚደረግባቸው የመንግስት እቅዶች ላይ በስፋት ማብራሪያ ሰጥተዋል።