በኦሮሚያ በቀጣዮቹ አራት ዓመታት የሚተገበር የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፕሮግራም ይፋ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ በቀጣዮቹ አራት ዓመታት የሚተገበር የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፕሮግራም ይፋ ተደረገ
አዳማ፣ መስከረም 25/2013(ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል አምስት ዞኖች ለቀጣይ አራት ዓመታት በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ የሚሆን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፕሮግራም ይፋ ተደረገ።
ፕሮግራሙ ይፋ የተደረገው የአውሮፓ ህብረት በመደበው ገንዘብ በክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራርን እስከታችኛው የአስተዳደር እርከን ለማውረድ የሚያስችል የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ በተካሄደበት ወቅት ነው።
በአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ኮሚሽን አማካሪ ዶክተር ጉቱ ቴሶ እንዳሉት ህብረቱ በክልሉ የአደጋ ስጋት ለመቀነስ፣ አሰራሩንና የአመራር ስራን እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን ለማውረድ ለሚካሄደው ፕሮግራም ከ7 ሚሊዮን 800ሺህ በላይ ዩሮ ተመድቧል።
ገንዘቡ በአደጋ ስጋት ቅነሳ፣ የአሰራር ማሻሻያና አቅም ግንባታ ስራ የሚውል መሆኑን አመልክተዋል።
በዚህም ለቀጣይ አራት ዓመታት የሚቆይ የአደጋ ስጋት አመራር ስራ በክልሉ 5 ዞኖች በሙከራ ደረጃ ለማካሄድ ፕሮግራሙ ዛሬ ይፋ መደረጉን አስታውቀዋል።
በህብረቱ ድጋፍ በሀገሪቱ ከቀበሌ ማህበረሰብ ደረጃ እስከ ፌዴራል ድረስ ወጥ የሆነ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፕሮግራም እንዲኖራት በአሰራር ማሻሻያና አቅም ግንባታ ላይ እየተሰራ መሆኑን ዶክተር ጉቱ አስረድተዋል።
ከቴክኒካል ድጋፍ በተጨማሪ ተጎጂዎችም ሆነ ማህበረሰቡ በአደጋ ስጋት ፖሊስና ስትራቴጂ ላይ በቂ ግንዛቤ፣ ክህሎትና እውቀት እንዲኖራቸው በተለይ በዞን፣ ወረዳና ከተሞች የአደጋ ስጋት አሰራርና አደረጃጀት እንዲኖር ለመጀመሪያ ጊዜ ከክልሎች ጋር ፕሮግራም ቀርፀን ወደ ተግባር ገብተናል ብለዋል።
በተመሳሳይ ለሱማሌ፣አማራ፣ደቡብና ሲዳማ ክልሎች አቅም ግንባታና የአሰራር ማሻሻያ ፕሮግራም የሚውል ድጋፍ እንደሚደረግም ገልጸዋል።
የአሮሚያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አቶ አባዲር አብዳ በበኩላቸው በክልሉ የአደጋ ስጋትን ለመቀነስና አሰራሮችን እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን ድረስ ለማውረድ እየሰራን ነው ብለዋል።
ይህም በክልልና በፌዴራል ደረጃ ብቻ ያለውን አሰራርና አደረጃጀት እስከ ወረዳና ማህበረሰብ ድረስ ለማውረድ መሆኑን አመልክተዋል።
በአደጋ ቅድመ ትንብያ፣ ማስጠንቀቂያና ከተከሰተም አሰራሩ ወደ መሬት ወርዶ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥበት እንደሆነም አስረድተዋል።
በዚህም የአውሮፓ ህብረት ለተያዘው የበጀት ዓመት ብቻ በተለይ ለአቅም ግንባታ፣ እናቶች በንፅህና የመጠጥ ውሃ እጥረት እንዳይጎዱ የውሃ ተቋማትና መሰረተ ልማት ዝርጋታ የሚያግዝ 92 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ሴቶች በአማራጭ የገቢ ምንጭ እንዲሰማሩ በቂ ስልጠናና አቅም ግንባታ እንዲያገኙ በትብብር እንሰራለን ብለዋል።
ፕሮግራሙ ይፋ ለማድረግ በተዘጋጀው የምክክር መድረክ የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የስራ ኃላፊዎችና ባለደርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።