ቀጥታ፡

10 ሚሊዮን ብር ወጪ የሆነበት 40 ሺህ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ድጋፍ አደረገ--የአፍሪካ ቀንድ የአስቸኳይ ጊዜ ግብረ ኃይል

አዲስ አበባ መስከረም 25/2013 (ኢዜአ) የአፍሪካ ቀንድ የአስቸኳይ ጊዜ ግብረ ኃይል 10 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት 40 ሺህ ኬ.ኤን-5 የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ድጋፍ አበረከተ። 

የግብረ ኃይሉ ሊቀመንበር ዶክተር ፉሃሚ ሞሃመድ ድጋፉን ለጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ አስረክዋል።

ዶክተር ደረጀ የተደረገው ድጋፍ የወረርሽኙ ስርጭት በሰፋበትና ኬ.ኤን-5 የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንደ አገር እጥረት እያጋጠመ ባለበት ወቅት በመሆኑ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

ዶክተር ፉሃሚ የበጎ አድራጎት ግብረ ኃይሉ ኮቪድ-19 በዓለም አቀፍ ደረጃ መከሰቱን ተከትሎ ለአፍሪካ ቀንድ ምላሽ መስጠትን አልሞ የተቋቋመ ነው ብለዋል።

ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ለሚከሰቱ የግብዓትና የባለሙያ እጥረቶቸ በበጎ ፈቃድ በማሰባሰብና በማሰማራት አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱንም አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ በአፋር ክልል በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለመርዳትና መልሶ ለማቋቋም 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ በተለያየ መልኩ ማድረጉን ገልጸዋል።

በዛሬው የሁለተኛ ዙር መርሃ ግብርም 10 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበትን 40 ሺህ ኬ.ኤን-5 የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ድጋፍ መደረጉን አክለዋል።

ይህም የወረርሽኙን መስፋፋት ተከትሎ የጤና ባለሙያዎችን ተጋላጭነት ለመቀነስ እንደሆነም ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው የጭምብል ድጋፉ በአገር አቀፍ ደረጃ እጥረት እየተከሰተ ባለበት ወቅት በመሆኑ እገዛው የጎላ ነው ብለዋል።

የወረርሽኙን መስፋፋት ተከትሎ የጤና ባለሙያዎች አሁንም ተጋላጭ መሆናቸውንን በመጠቆም።

በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንም ከመንግስትና ከጤና ባለሙያዎች ጎን በመሆን መሰል ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ግብረ ኃይሉ ወረርሽኙ በተከሰተበት ወቅት ምላሽ ለመስጠት መቋቋሙ ለአገር ያለውን አለኝታነት ያሳየበት በመሆኑ አድንቀው እያበረከተ ላለው አስተዋጽኦና ለበጎ አድራጎት ስራው ምስጋና ቸረዋል።

ጭምብሎቹ አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎች እንደ ክልሎቹ የስርጭት ምጣኔ የሚከፋፈል መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል።

በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ በድጋፉ ለተሳተፉ አካላትና ተቋማት የምስጋናና የእውቅና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም