ቀጥታ፡

በእጃቸው ከ100 ሺህ እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር አሮጌ ኖቶች ያላቸው ግለሰቦች በፍጥነት እንዲቀየሩ ባንኩ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣መስከረም 25/2013 (ኢዜአ) በእጃቸው ከ100 ሺህ እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ያላቸው ግለሰቦች ኖቶቹን እስከ ጥቅምት 6 ቀን 2013 እንዲ ቀይሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ።

ኢትዮጵያ ነባሮቹን የ10፣ የ50ና የባለ 100 ብር ኖቶችን መቀየር የጀመረች ሲሆን፤አዲስ ባለ 200 ብር ኖት ወደ ሥራ ማስገባቷ ይታወቃል።

ከ100 ሺህ ብር በላይ ያላቸው ሰዎች በአንድ ወር፤ ከ100 ሺህ ብር በታች ያላቸው ሰዎች እስከ ሶስት ወር ባለው ጊዜ ኖቶቹን እንዲቀይሩ የጊዜ ገደብ መቀመጡ አይዘነጋም።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባሰራጨው በአጭር የጽሁፍ መልዕክት እንዳስታወቀው ከ100 ሺህ እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የአሮጌ ኖቶች የመቀየሪያ ጊዜ ጥቅምት 6 ቀን 2013 ያበቃል።

በእጃቸው የተጠቀሰው መጠን ገንዘብ ያላቸው ሰዎች በተቀሩት 11 ቀናት ገንዘቡን እንዲቀይሩ አሳስቧል።

ኢትዮጵያ አዲሱን የብር ኖቶች 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ያሳተመች ሲሆን፤ ኖቶቹን ለማሳተም 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወጪ አድርጋለች።

ወደ ስርጭት በመግባት ላይ ያሉት የብር ኖቶች በጠቅላላ 262 ቢሊዮን ብር ዋጋ አላቸው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ በሳምንቱ መጨረሻ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ ኖቶቹን  መቀየር ከተጀመረ በ14 ቀናት ውስጥ ከባንክ ውጭ የነበረ 14 ቢሊዮን ብር ወደ ባንክ ገቢ ሆኗል።

በዚሁ ጊዜ ውስጥ  580 ሺህ ዜጎች አዲስ የባንክ ሂሳብ (አካውንት) መክፈታቸውን ተናግረዋል።

በአገሪቱ በዝውውር ላይ የነበረው የአምስት ብር ኖት ባለበት እንዲቀጥል ተወስኗል።ኖቱ ወደፊት ወደ ሣንቲም እንደሚቀየር  ባንኩ መግለጹ ይታወሳል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም