ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና የሕዝቦቿ ዕጣ-ፈንታ የሚቃናው በውጤታማና በጥንቃቄ በሚታነጽ የዴሞክራሲ ግንባታ ነው

አዲስ አበባ፣መስከረም 25/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያና የሕዝቦቿ ዕጣ-ፈንታ የሚቃናው በውጤታማና በጥንቃቄ በሚታነጽ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሆኑን ፕሬዚደንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ፡፡

ፕሬዚዳንቷ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባ መክፈቻ ላይ በመገኘት መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም ዴሞክራሲ በፍላጎት ብቻ ሳይሆን እንደ አስፈላጊነቱ ዋጋ በመክፈል ጭምር የሚገነባ ነው ብለዋል።

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ሆደ ሰፊነት፣ አስተዋይነት፣ ምክንያታዊነትና ከፍተኛ ጽናትን እንደሚጠይቅም አውስተዋል።

መብትና ግዴታ የዴሞክራሲ ሁለት ክንፎች መሆናቸውን ያወሱት ፕሬዚዳንቷ "ዴሞክራሲ የመብት ብቻ ሳይሆን የግዴታና የኃላፊነት ጉዳይ ጭምር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል" ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የተከሰቱ የሕግ ጥሰቶች የዜጎችን ሕይወትና ንብረት የቀጠፉ አስነዋሪ ተግባራት የዴሞክራሲ አረዳድ ምን ያህል በስህተቶች የተሞላ እንደሆነ በቂ ማሳያ እንደነበርም ፕሬዚደንቷ ተናግረዋል።

"ወይ ሁላችንም በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንሄዳለን ካልሆነም ማናችንም አንሄድም" ያሉት ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዴሞክራሲ የሁሉንም አስተዋጽኦና መስዋዕትነት እንደሚፈልግም አመላክተዋል።

እውነትን በአግባቡ ተረድቶ ሁሉም በኃላፊነትና በሰለጠነ መንገድ ካልተጓዘ በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚውም እንደ አገር የሚፈለገውን ስኬት መጎናጸፍ እንደሚያስቸግርም አስገንዝበዋል።

ዴሞክራሲን ከሕግ የበላይነትና ከዜጎች ዲሲፕሊን ነጥሎ ማየት እንደማይቻል የገለጹት ፕሬዚዳንቷ "የሕግ የበላይነት መረጋገጥ ለሁሉም ዜጎች እኩል፣ ሠላማዊና ምቹ የዴሞክራሲ ምህዳር እንዲፈጠር ያደርጋል" ብለዋል።

ዲሲፕሊንም ዜጎች በተፈጠረላቸው ምህዳር በሰለጠነ መንገድ እንዲሳተፉ ዕድል ለመፍጠር ምቹ አጋጣሚ መሆኑን አክለዋል።

በተያዘው ዓመትም ፖለቲከኞችና ዜጎች ዴሞክራሲን በባዶ ከመሻት ባለፈ የሚጠይቀውን ሥርዓትና ዲሲፕሊን እንዲላበሱ ለማድረግ ከፍተኛ ስራዎች እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።

መጪው አገራዊ ምርጫ ሠላማዊና ዴሞክራሲዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የዴሞክራሲ ልምምዶች በሥርዓት የሚካሄዱና በሕግ የበላይነት የሚመሩ መሆን እንደሚኖርባቸውም ገልጸዋል።

በዚህ ዓመት የዴሞክራሲ ሥርዓት በቂ መደላድል ለማዘጋጀትና የፖለቲካ መበልጸግን ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የሚስተዋሉ ጉድለቶችን በማረም ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ ከተሳትፎም ሆነ ከፉክክር የሕዝቦችን ዴሞክራሲያዊ መሻት የሚያረካና ዓለምዓቀፋዊ መመዘኛዎችን የሚያሟላ መሆን እንደሚኖርበትም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ፓርላማው የተለያዩ የፖለቲካ ድምጾች የሚሰሙበትና ፓርቲዎች አንጻራዊ ውክልና የሚያገኙበት እንዲሆን ፍትሃዊ የፉክክር ሜዳ ለመፍጠርና የፖለቲካ ምህዳሩን ምቹ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም