የጥበብ ውጤቶች ለሕዝቦች የበለጠ መቀራረብ የተሻሉ መንገዶች ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የጥበብ ውጤቶች ለሕዝቦች የበለጠ መቀራረብ የተሻሉ መንገዶች ናቸው
አዲስ አበባ፣መስከረም 25/2013 (ኢዜአ) የተለያየ ባሕል፣ ማንነትና ገፅታ ያላቸውን ሕዝቦች የጥበብ ውጤቶችን በመጠቀም ይበልጥ ማቀራረብ እንደሚቻል ተነገረ።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች ራሳቸውን የሚገልጹባቸው የተለያዩ ባህል፣ ማንነትና ገጽታን የተላበሱ መሆናቸው እሙን ነው።
ይሁን እንጂ እነዚህን የየራሳቸውን መለያዎችና መገለጫዎች እምብዛም ሲያስተዋውቁ አይስተዋሉም።
ሰሞኑን ዓመታዊውን የኢሬቻ በዓል ምክንያት ያደረገና ይህን ክፍተት ለመድፈን ይረዳል የተባለ የሙዚቃ፣ የፋሽን፣ የስዕልና የስነ-ግጥም መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር።
ኢዜአ ያነጋገራቸው በመርሃ ግብሩ የተሳተፉ በዘርፉ የተሰማሩ ወጣቶች ጥበብ አንዱ ሌላውን የሚያውቅበት ቀላል መንገድ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
የጥበብ ባለሙያው ወጣት ብሩክ ግርማ 'ጥበብ ለበጎ ነገር ጥቅም ላይ ከዋለ ሕዝቦችን ያቀራርባል፣ አገር ይገነባል' ይላል።
የጥበብ መንገድ ሠላማዊ በመሆኑ ሕዝቦችን በገንቢ መንገድ መተቸት፣ ማስተማርና ማቀራረብ የሚያስችል ነው ሲል ገልጿል።
አገራዊ አንድነትን፣ ሠላምን፣ ፍቅርንና ኢትዮጵያዊነትን ማስረጽ የሚያስችል አቅም እንዳለውም ተናግሯል።
በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ ያለውን ኢሬቻን ጨምሮ ሌሎችም ክብረ በዓላት የአንድ ቡድን ብቻ ሆነው መታሰብና መታጠር እንደሌለባቸውም ነው የተናገረው።
የሁነት አዘጋጇ ወጣት ብርቱካን ሚደቅሳም 'የጥበብ መንገድ በተሻለ መልኩ ሕዝቦችን ማገናኛ መንገድ ነው' ትላለች።
"ኢትዮጵያዊያን ብዙ ነገራችንን በጥበብ የምንገልጽ እንደመሆናችን ሕዝቦችን በማቀራረብ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው" ስትልም አክላለች።
የኦሮሞ ባሕላዊ ምግቦችን በማዘጋጀት በአንድ በኩል ገቢ እያገኘች በሌላው ደግሞ ባሕሉን እያስተዋወቀች መሆኗን የገለጸችው ደግሞ ወጣት ረቢፈን አሰፋ ናት።
ወጣቷ የአንድ ሕዝብ የምግብ አሰራር ዘይቤ እንደ ጥበብ ሁሉ ማንነቱን መግለጫና ማንጸባረቂያ መንገድ ነው ትላለች።
በዚህ መንገድ አንዱን ሕዝብ ከሌላው ጋር ማስተዋወቅና ማቀራረብ እንደሚቻል የወጣት ረቢፈን እምነት ነው።
"ጥበብ የማናውቀውን ሕዝብ በቀላሉ የምናውቀበት አንዱ መንገድ ነው" በማለት የወጣቶቹን ሃሳብ የሚጋራው ደግሞ የመድረክ አስተባባሪ ገመዳ ኦላና ነው።
እንደ ወጣቱ ገለጻ ጥበብ ሕዝቦችን ያቀራርባል፤ የሕዝቦች መቀራረብ ደግሞ ሠላምና አብሮነትን ያሰፍናል።