የወንድማማች ሕዝቦች ጽኑ ፍቅር!

83
አዲሱ ረታ ኢዜአ ሐምሌ 7 2010 ዓ.ም ሐምሌ ሰባት  ካዛንቺስ ራዲሰን ብሉ ሆቴል በር ላይ ነው። ስድስት ዕድሜያቸው ሃያዎች ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች በራሳቸው ግጥም ያዛሜሉ፤ ፊታቸው ፈክቷል፤ ደስታ በደስታ ሆነዋል።የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድና የፕሬዚዳንት ኢሳይስ አፈወርቂ ፎቶ የታተመበት ቲሸርት ለብሰዋል። የኤርትራን ሰንደቅ ዓላማ ተቀባብለው በስሜት ያውለበልባሉ። እንደገና ይዘምራሉ። "ለበጎ ከሆነ ለቁም ነገር ጉዳይ ጎረቤት ወዳድ ነን እንግዳ ተቀባይ . . . አሁንም እየተቀባበሉ ያዜማሉ። ስንደመር አንድ እንሆናል ስንደመር ብዙ እንሆናለን። ይህ ታሪካዊ ቀን እውነትም ታሪካዊ ነው የሚያስብሉ ብዙ ክስተቶች ነበሩት። በእርግጥ ባለፈው ሳምነት ሌላ ልዩ ታሪክ ተበስሯል። ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የጥሉን ግርግዳ በፍቅር በማፍረስ ወደ አስመራ አቅንተው በደማቅ ቀለም ታሪክ ጽፈዋል። ይህ ታሪክ በድርሳን ሲከተብ . . . ኤርትራያውያን የናፈቁትን ወዳጅ፣ ዘመዶቻቸውን ወክለው ወደ አስመራ ያቀኑትን ኢትዮጵያውያን በፍጹም ልባዊ ፍቅር በአደባባይ ወጥተው ተቀብለዋል። ኢትዮጵያውያንም ''እኔም ኤርትራውያን ወንድሞቼ እጅግ ናፍቀውኛል'' በማለት ማንም ቀስቃሽ ሳያስፈልገው በአዲስ አበባ ጎዳና ላይ ተምሞ ከወደ ሰሜን ላሉ ወንድሞቹ ያለውን ክብርና ፍቅር እጅግ በሚያስደንቅ ሁኔታ አሳይቷል። ሐምሌ ታሪክ ቀያሪ ሆናለች። ሁለት ሊለያዩ የማይችሉ፣ ከልዩነት ይልቅ አንድነታቸው ተራራ የሚያክል ህዝቦች ለ20 ዓመታት ገደማ ተኳርፈው ቆይተዋል። ተራርቆ የነበረው ህዝብ በመሓሉ ያለችውን ትንሿዋን ልዩነቱን ሊያጎላ ሲሞክር ተስተውሏል። የመራረቁ ምክንያት ምንም ይሁን ምን የሰፋው ልዩነት ጠቦ ህዝቡ የጥሉን ግርግዳ አፍርሷል፤ ፍቅር አሸንፏል። በእኔ ግምት እንዲህ ዓይነት ምናልባት በክፍለ ዘመናት ወይም ደግሞ በጭራሽ ላያጋጥም ይችላል። እጅግ ብዙ እውቅ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት የእንግዳ አቀባበል ስነ ስርዓት የተከናወነበት ዕለት ነውና። 170 ገዳማ የመገናኛ ብዙሃን ሙያተኞች የዘገባ ሽፋን ለመስጠት የተመዘገቡበትም ክስተት ነው። ገና ከዋዜማው ጀምሮ እጅግ በተጨናነቀ መልኩ ሲከናወን የነበረው የመገናኛ ብዙሃን ሙያተኞች የዘገባ ሽፋን ፍቃድና ይለፍ አሰጠጥ ጉዳይ አንዱ ማሳያ ነው። ሁሉም ሙያተኞች በጉጉት ይህን ታራካዊ ቀን የዘገባ ሽፋን እንዲያገኝ ለማስቻል እጅግ ጓግተዋል። ለዚህም ይመስላል አብዛኛው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያ ከሌሊቱ 10:30 ሰዓት ጀምሮ በቦሌ ዓለም ዓቀፍ አየር ማራፊያ የተገኘው። ያንን ሁሉ ብርድ ችሎ እንግዳውን ተቀብሏል። ሌላው በዚህ ቀን ሊረሳ የማይችለው ጉዳይ ፕሬዚዳንት ኢሳያስን አፈወርቄን ለመቀበል የአንጋፋው ብሔራዊ ትያትር የባህል ቡድን፣ የኦሮሞ ባህል ማዕከል የባህል ቡድን፣ የፖሊስ ማርሽ፣ የኃይማኖት አባቶች በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ዘማሪዎች ደማቅ የዝማሬ ስነ ስርዓት አከናውነዋል። ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን የወሰድን እንደሆነ የፌዴራል መንግስት ሚኒስትሮች፣ የክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች እንዲሁም አንጋፋና ታዋቂ ግለሰቦችና የኪነ ጥበብ ሙያተኞች አምረውና ተውበው ለኤርትራ ህዝብ ያላቸውን ፍቅር በይፋ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን በመገኘት ፕሬዚዳንቱን ተቀብለዋል። መቼም የአዲስ አበባ ነዋሪ ምን ያህል ኤርትራውያንን እንደሚወድ በተግባር አረጋግጧል። አዲስ አበቤዎች በነቂስ ወጥተው ኤርትራውያን ውንድሞቹን ''እኛ አንድ ሕዝብ ነን፤ አንለያይም'' ሲል ተደምጧል። ከቤተ መንግስት እስከ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ መግቢያ በር ድረስ አዲስ አበቤዎች በዋናው መንገድ ዳርና ዳር ተሰልፈው የደስታ ስሜታቸውን በሲቃ ገልጸዋል። ፕሬዚዳንቱን ለመቀበል የወጣው ነዋሪ አገሩን እንደሚወድ ጎሬቤቱን እንደሚወድ ይዞት በወጣው መፈክሮች ገልጿል። በተለይ ደግሞ ለወንድም የኤርትራ ህዝብ ያለውን አክብሮት የተለያዩ ግጥሞችን ፈጥሮ ከዜማ አዋህዶ ሲያዜም ውሏል። ከዚህ ጎን ለጎን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን የሚያሞግሱ መፈክሮች በሰፊው ተደምጠዋል። እኔ በበኩሌ ለዘመናት አብሮ ክፉ ደጉን አሳልፎ የሚያውቅ ህዝብ ይቅርና በጉርብትና ብቻ የኖረን ህዝብ መለያየት እንደማይቻል ተረድቼያለሁ። በወጣቱ ትውልድ ዘንድ አምባገንን ተደርገው የተሳሉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አገሮቹ ግንኙነታቸውን ማደስ ሲጀምሩ የፊታቸው ላይ ይነበብ የነበረው ደስታና ሳቃቸው ብዙሃንን አስገርሟል። የሆነው ሆኖ ከዚህ ሁሉ ዓመታት በኃላ በእነዚህ ሁለት ህዝቦች መካከል ያለው የአንድነት ገመድ በቀላሉ የማይበጠስና ጽኑ መሆኑን በግልጽ ያሳየ ክስተት ተፈጥሯል። ሰላም ለወዳጅ ለሁለቱ አገሮች ህዝቦች።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም