በሕዳሴው ግድብ ላይ ሰፊ ተደራሽነት ያለው ዓለምአቀፍ የዲፕሎማሲ ሥራ ይሰራል -ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
በሕዳሴው ግድብ ላይ ሰፊ ተደራሽነት ያለው ዓለምአቀፍ የዲፕሎማሲ ሥራ ይሰራል -ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 25/2013 ( ኢዜአ) በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ሰፊ ተደራሽነት ያለው ዓለምአቀፍ የዲፕሎማሲ ሥራ እንደሚሰራ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለፁ።
የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ የመክፈቻ ስብሰባቸውን ዛሬ አካሂደዋል።
በዚህ ወቅት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብ የተከተለችው የድርድር መርህ የተፋሰሱን አገራት ሳትጎዳ የራሷን ጥቅምና ክብር የሚያስጠብቅ ነው።
ግድቡን በተመለከተ በአገሪቱ ካሉ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች፣ ምሁራን፣ ፓለቲከኞችና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይትና ምክክር ሲደረግ መቆየቱንም ፕሬዚዳንቷ አስታውሰዋል።
ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የዲፕሎማሲ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው፤ በዚህ ዓመትም ሰፊ ተደራሽነት ያለው የዲፕሎማሲ ሥራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
ያለፈው ዓመት የሕዳሴው የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት የተጠናቀቀበትና ለግድቡ ከፍተኛ የቦንድ ግዥና ድጋፍ የተደረገበት እንደነበረም ተናግረዋል።
አዲሱ ዓመት የሕዳሴው ግድብ በሁለት ተርባይን ኃይል የማመንጨት ሥራ እንደሚጀምርና ሁለተኛው ምዕራፍ የውሃ ሙሌት የሚደረግበት መሆኑንም ፕሬዚዳንቷ አመላክተዋል።
በሌላ በኩል መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ለሚያከናውናቸው ተግባራት ህዝቡ የበኩሉን እንዲወጣና ለህግ የበላይነት ዘብ እንዲቆም አስገንዝበዋል።
በአዲሱ ዓመት የተያዙ ዕቅዶች እንዲሳኩ ሁሉም አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ጥሪ አቅርበዋል።