ከኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ሰላም፣ ፍቅርና አንድነትን የሚሰብኩ ስራዎች ይጠበቃሉ - ኢዜአ አማርኛ
ከኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ሰላም፣ ፍቅርና አንድነትን የሚሰብኩ ስራዎች ይጠበቃሉ
አዲስ አበባ ሀምሌ 7/2010 የኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነትና፣ መተሳሰብን የሚሰብኩ መልዕክቶችን በማስተላለፍ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ። የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት አስመልክቶ እሁድ በሚሌኒየም አዳራሽ የኪነ-ጥበብ መርሃ-ግብር ይካሄዳል። በዚህም 25 ሺህ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚገኙ የሚጠበቅ ሲሆን የሁለቱን አገራት ሰላም ማብሰሪያ መርሃ-ግብር በኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች እንደሚካሄድ ይጠበቃል። በመርሃ-ግብሩ ተሳታፊ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችም ሆኑ የጸጥታ አካላት በጸጥታው ጉዳይ ላይ ተቀራርበውና ተናበው ሊሰሩ እንደሚገባም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገልጸዋል። ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት በአገር ሰላም እንዲሰፍንና ዕድገት እንዲኖር እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል ኃላፊነት አለበት። በተለይም የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በስራዎቻቸው ላይ ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነትና፣ መተሳሰብን የሚሰብኩ መልዕክቶችን ማስተላለፍ ይገባቸዋል ብለዋል። ወይዘሮ ሒሩት ታደለ የተባሉ ነዋሪ በሰጡት አስተያየት የኪነጥበብ ባለሙያዎች በሰላም ዙሪያ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡ ሌላው አስተያየት ሰጪ ወጣት ቴዎድሮስ ምንዳ በበኩሉ የሁለቱን ሀገራት ነዋሪዎች ፍቅር የሚያጠናክሩና ህዝብ ለህዝብ የሚያስተሳስሩ ኪናዊ ዝግጅቶችን በማቅረብ ረገድ ከኪነጥበብ ባለሙያዎች ብዙ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡ የተጀመረውን መልካው ጉዞ ለማደናቀፍ የሚጥሩ አካላት ሊኖሩ ስለሚችሉ ህብረተሰቡ በጥንቃቄና በንቃት እንዲጠብቅና ከጸጥታ አካላት ጋር ተባብሮ እንዲሰራ መልዕክት አስተላልፈዋል።