ቀጥታ፡

ለሰለጠነ የፓለቲካ ባህል መጎልበት የፓርቲዎች ውይይት ሊጠናክር ይገባል

መስከረም 25/2013 (ኢዜአ)  በኢትዮጵያ  የሰለጠነ የፓለቲካ ባህልን ለማጎልበት የፖለቲካ ፓርቲዎች  ውይይት ሊጠናክር  እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሀሳብ አመንጪነት በአገሪቷ የሚንቀሳሰቁ ፓርቲዎች ውይይት መጀመራቸው ይታወሳል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የገለጹ ፓርቲዎች እንደተናገሩት በአገሪቱ በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል የተጀመሩት ውይይቶች  የትብብር መንፈስን ለማጠናከር አስፈላጊ ናቸው።

እንደዚህ አይነት መድረኮች ቀጣይነት ሊኖራቸው እንደሚገባም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ  በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረጉ ውይይቶች ጥሩ ጅማሮ መሆኑን ገልጸው፤ ሀሳብን ለማቀራረብና ወደ ተሻለ ነገር ለማምጣት የሚያሰችል የሰለጠነ አካሄድ ነው ብለዋል።

ውይይቶቹ ፓርቲዎች በሰላም፣ በጸጥታ፣ በልማትና በሌሎች ለአገር ጠቃሚ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል መንገድ እንደሚፈጠጥር ገልጸዋል።

አገሪቱን ከድህነት ለማውጣትና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት የሚያስችሉ የልማት አቅጣጫዎችን በጋራ ለመንደፍ ወሳኝ መሆኑንም አክለዋል።

ዶክተር ጫኔ እንደገለጹት በፓርቲዎቹ መካከል የተጀመረው የሀሳብ መንሸራሸር ከቀጠለና ፓርቲዎች በኩል ቁርጠኝነቱና ሀቀኝነቱ ካለ የሰለጠነ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር ያስችላል።

መጪው አገራዊ  ምርጫ ተዓማኒ፣ ዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ ለማድረግም የፓርቲዎች የትብብር መንፈስና መግባባት ወሳኝ ነው ሲሉም ተናግረዋል። 

ለዚህም የፓርቲዎቹ ቀጣይነት ያለው ውይይት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።

ቀደም ሲል በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል የተደረገው የቃል ኪዳን ሰነድ ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግም ዶክተር ጫኔ ተናግረዋል።

በምርጫ ቦርድ በኩልም በተለያዩ መመሪያዎችና አዋጆች ላይ ያተኮሩ ውይይቶች  ቀጣይነት ባለው መልኩ ሊካሄዱ እንደሚገባ አክለዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ዘሪሁን ገብረግዚአብሔር በበኩላቸው  ውይይቶቹ ተራርቀው የነበሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአንድ ጠረጴዛ ተቀምጠው ለህዝቡ አማራጮችን እንዲያስቀምጡ ያስችላል ሲሉ ተናግረዋል።

 የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን አማራጭ ርዕዮተ አለም ለህዝቡ   የሚያስተዋውቁበትንና ህዝቡ  የተሻለውን የሚለይበት እድልን ማስፋት ያስችላል ነው ያሉት፡፡

ሆኖም ውይይቶቹ ፓርቲዎችን በእኩልነት ተሳታፊ ማድረግ እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።

እንደ አቶ ዘሪሁን ገለጻ አገራዊ መግባባት ማጎልበት የሚቻለው ሁሉም አካላትን አሳታፊና አካታች ማድረግ ሲቻል ነው ።  

የህግ የበላይነት ለማስፈንና እርቅና ሰላም ለማውረድ እኩልነትና አሳታፊነት አስፈላጊ ነው ሲሉም ተናግረዋል።  

መጪው አገራዊ ምርጫንም በሰላምና መረጋጋት ለማካሄድ የፓርቲዎቹ ውይይትና አንድነት ወሳኝ መሆኑን አክለዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትም ለሁሉም ፓርቲዎች ሀሳባቸውን የሚገልጹበት መድረክ ከወዲሁ በእኩልነት ሊሰጥ እንደሚገባም ነው የገለጹት።

የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን ታፈሰ በክልልና አገር አቀፍ ፓርቲዎች መካከል የተጀመረው ውይይት ፓርቲዎች ተቀራርበው ለአገሪቱ ጠቃሚ የሆኑ ጉዳዮች ላይ  እንዲመክሩ እድል መፍጠሩን ገልጸው፣ ይህም የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ያሰችላል ብለዋል።

በፓርቲዎች መካከል መልካም ግንኙነት እንዲጎለብት አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት።

በመሆኑም ውይይቶቹ ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዘብዋል።

በቀጣይም በአገሪቱ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ አገራዊ ምርጫ ለማድረግ ውይይቶቹ  ፋይዳ እንደሚኖራቸው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም