ቀጥታ፡

ብልጽግና ፓርቲ ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል በሙሉ አቅሙ ይሰራል---አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ

አዳማ፣ መስከረም 25/2013 (ኢዜአ) ብልጽግና ፓርቲ ሀገራዊ ለውጡን በማስቀጠል ለህብረ ብሄራዊ አንድነት፣ እኩልነትና እውነተኛ ዴሞክራሲ ግንባታ በሙሉ አቅሙ እየሰራ መሆኑን የፓርቲው የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ ገለጹ።

ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ  የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ዘርፍ አመራሮች የተሳተፉበት የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አቶ ተስፋዬ  ለውጡ በሀገሪቱ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚነሱትን የፖለቲካ ጥያቄዎች የሚመልሱ ፍትህ፣ እኩልነት፣ ህብረ ብሄራዊ አንድነትና እውነተኛ ዴሞክራሲ የሚያረጋግጡ እና የሚመልሱ ናቸው ብለዋል።

ፓርቲው የራሱ መለያ እሴቶች የሆኑትን በተለይ  ለህብረ ብሄራዊ አንድነት፣ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት የዜጎች እኩልነት፣ እውነተኛ ፌዴራሊዝምና ዴሞክራሲን ማረጋገጥ በሙሉ አቅሙ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

"ሀገሪቱ አሁን የያዘችውን የብልጽግና ጉዞ አጠናክራ ትቀጥላለች" ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ ፅንፈኝነት መሰረት ያደረጉ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ለውጥን ማደናቀፍ እንደማይችሉ ተናግረዋል።

ለውጡን ተቋማዊ አድርጎ ከመንቀሳቀስ አንፃር የሚታዩ ክፍተቶችን በማረም ሀገራዊ የብልፅግና ጉዞን እናረጋግጣለን ብለዋል።

በመድረኩ  የ2012 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም እና የተያዘው የስራ ዘመን  ዕቅድ ዙሪያ  ውይይት እንደሚደረግ  ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም