የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃዎች አገልግሎትን ለማዘመንና ህገ ወጥ አሰራሮችን ለመከላከል እየሰራ ነው --- የአስተዳደር የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ - ኢዜአ አማርኛ
የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃዎች አገልግሎትን ለማዘመንና ህገ ወጥ አሰራሮችን ለመከላከል እየሰራ ነው --- የአስተዳደር የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ
አዲስ አበባ መስከረም 24/2013(ኢዜአ) የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃዎች አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመንና ህገ ወጥ አሰራሮችን ለመከላከል እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ገለጸ፡፡
የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ አብዱራሂም እንደገለፁት በኤጀንሲው ከቅርብ ግዜ ወዲህ በወረቀት ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት በኔትወርክ ሲስተም ለመተካት በዘመናዊ መልክ ስራዊችን ማከናወን ተጀምሯል።
አሁን ላይ እየተተገበረ ያለው የቴክኖሎጂ አሰራር በአግልግሎት አሰጣጡ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ ከፍተኛ ለውጥ ተመዝገቦበታል ብለዋል ።
የኩነት መረጃዎችን በኔትወርክ ሲስተም የመመዝገብ እንቅስቃሴ አሁን ላይ በከተማዋ 104 ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ መሆን መጀመሩን የገለጹት አቶ መሐመድ ፤በቀጣይም በቀሩት ጥቂት ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ ለማዳረስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ምን አልባት ኢንተርኔት ቢቋረጥ አገልግሎቱን ማግኘት የሚቻልበት የኦፍ ላይን አሰራር መዘርጋቱንም አመላክተዋል።
ይህ አሰራር ኢንተርኔት በማይኖርበት ወቅት አገልግሎት ፈላጊዎች በሚመጡበት ጊዜ መዝግቦ ኔትወርኩ ባለበት ጊዜ ወደ ሲስተሙ የሚገባበት አሰራር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህ የኦፍላን አሰራርም ባሁኑ ወቅት በ89 ወረዳዎች ተግባራዊ መሆን የጀመረ ሲሆን እስከ መስከረም 30 ቀን 2013 ድረስ በሁሉም ወረዳዎች አሰራሩ ተዘርግቶ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።
ሌላኛው ተቋሙ ማሻሻያ ካደረገባቸው አሰራሮች መካከል ህገ ወጥ ሀሰተኛ ማስረጃዎችን መከላከል ነው፡፡
ከተቋሙ የሚወጡ ሰርትፊኬቶችን ደህንነት ለመጠበቅ አገልግሎቱን ዲጅታል ማድረግ የሚያስችል አሰራርን ለመከተል እየተሰራ መሆኑን አቶ መሐመድ አብዱራሂም ተናግረዋል።
በወሳኝ ኩነቶች ማለትም በልደት፣ በሞት፣በጋብቻ እና በፍች ሰርፍኬቶች ላይ የሚያጋጥመውን ችግር ለመለየትና ለመቆጣጠር የሚያስችል የሴኩሪቲ ፕሪንተር ቴክኖሎጂ ግዥ ለመፈጸም በሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቴክኖሎጂው ከብልሹ አሰራር እና ተመሳስለው ከሚሰሩ የኩነት ሰርተፍኬቶች እንደሚከላከል በመግለጽ በቅርቡም ግዥው ተፈጽሞ ወደስራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ዘመናዊ የወሳኝ ኩነት መረጃ አያያዝ ከራሱ ከኤጀንሲው ባሻገር ከተማ አስተዳደሩ ለሚያወጣቸው እንደ ትምህርትና ጤና እና የመሳሰሉት ፖሊሲዎች ለግብዓትነት ስለሚጠቅም በቀጣይ አሰራሩን የማዘመን ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ መሐመድ አመላክተዋል።