ቀጥታ፡

ግጭት መፍጠር የሚፈልጉ አካላት ኢሬቻን ለማደናቀፍ ብዙ ጥረዋል- የኦሮሚያ ከልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ  መስከረም 24/2013 (ኢዜአ) ግጭት መፍጠር የሚፈልጉ አካላት የኢሬቻ በዓልን ለማደናቀፍ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም በህዝቡና የጸጥታ አካሉ ትብብር እቅዳቸው መክሸፉን የኦሮሚያ ከልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ ለሁለት ተከታታይ ቀናት የተከበረውን የኢሬቻ በዓል መጠናቀቅ አስመልክቶ ፕሬዚዳንቱ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በዓሉ እንዲደናቀፍ ለጥፋት የቆሙ ሃይሎች የተለያዩ ጥረቶችን ቢያደርጉም በህዝቡና የፀጥታ አካሉ ትብብር ጥረታቸው ሙሉ ለሙሉ  ከሽፏል ብለዋል።

የኢሬቻ በዓል በተለያዩ ፈተናዎች ዛሬ ላይ ደርሶ በተፈጠረው ለውጥ ምክንያት በአዲስ አበባም ለመከበር መብቃቱን ጠቁመዋል።

ከለውጡ በፊት ኢሬቻ እንዳይከበር ጥረቶች ሲደረጉ እንደነበርና ብዙ ጉዳቶችም መድረሳቸውን አስታውሰዋል።

ይህን ሲያደርጉ የነበሩ አካላት አሁን ላይ በአንድ በኩል የበዓሉ ተቆርቋሪ መስለው ቀርበው በስውር ደግሞ በዓሉን ለማደናቀፍ "ፈንጂ" ልከውብናል ብለዋል።

እነዚህ አካላት በአጭሩ "ጉዶች" ናቸው ያሉት ፕሬዝዳንቱ እኩይ ጥረታቸው ሁሉ በህዝቡና የጸጥታ ሃይሉ ትብብር ከሽፏል ብለዋል።

በመሆኑም ለህዝቡ፣ ለፀጥታ ሃይሉ፣ ለአባ ገዳዎችና ወጣቶች አጠቃላይ በዓሉ በሰላም እንዲከበር ጥረት ላደረጉ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም