ቀጥታ፡

በኢትዮ- ኤርትራ መካከል የተፈጠረው የሰላም ሂደት ብሄራዊ አንድነትን ለማጠናከር ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ተገለፀ

ሶዶ  አምሌ 7/2010 በኢትዮ- ኤርትራ መካከል የተፈጠረው የሰላም ሂደት በአገር ውስጥ የተጀመረውን ብሄራዊና ሃገራዊ አንድነት ለማጠናከር ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ተገለጸ፡፡ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ አባላትና የሶዶ ከተማ ወጣቶች እንደተናገሩት በሁለቱ ሃገራት መካከል የተጀመረው የሰላም ሂደት የሃገር ውስጥ ሰላምንና አንድነትን ለማጠናከር ይረዳል፡፡ ''የሰላም ሂደቱ ዘላቂ እንዲሆን ከመንግስት ጎን በመሆን እንሠራለን'' ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ የወላይታ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የድርጅት ጉዳይና የደቡብ ክልል ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተሰማ ባልቻ በስነ ልቦናና በአኗኗር ዜይቤ የማይለያይ ማህበረሰብ ከ20 ዓመታት በኋላ  በመጣዉ ለውጥ ደስታ ተሰምቷቸዋል፡፡ የሁለቱ ሃገራት መሪዎች ያወረዱትን ዕርቅና ሰላም ድርጅታቸው የሚደግፍና ለዘላቂነቱም የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሃገራቱ በመካከላቸው የፈጠሩት የሰላም ሂደት የተጀመረውን ብሄራዊና ሃገራዊ አንድነት ለማጠናከር ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ ''ሁለቱ የመንግስት ልዑካን ከሚያደርጉት ውይይት ባለፈ ምሁራን የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎቻቸው እንዲሁም ወጣቱን ያሳተፈ ህዝባዊ ውይይት ተጠናክሮ መቀጠል አለበትም'' ብለዋል፡፡ በፓርቲው የወላይታ ሶዶ ከተማ ተወካይ መምህር ፍቅሬ ሞሊሶ የሁለቱ ሃገራት መሪዎች ያለሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ያሳዩት ቁርጠኝነት ወንድማዊ ስሜትን ከማጎልበት ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ''ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ ይዘው የመጡት የመደመርና ሃገርን ለማረጋጋት የገቡትን ቃል ለመፈጸም እያደረጉ ያሉት ጥረት የሁሉም ዕገዛ ቢታከል ዘላቂነት ባለው መልኩ ሃገሪቱን ተጠቃሚ ያደርጋል'' ብለዋል፡፡ ''ሃገርን በጋራ አስተሳሰብ የበለጸገች ማድረግ ለመንግስት ብቻ የሚተው አይደለም'' ያሉት መምህር ፍቅሬ መከፋፈልን በማስቀረት ብሄራዊ ስሜትን ለማጎልበት የተጀመረውን ስራ ልዩነት ሳይኖር ለማስቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በሶዶ ከተማ የጎላ መንደር ነዋሪ ወጣት ታርኩ ጣሰው በኢትዮ- ኤርትራ መካከል የነበረውን ቁርሾ ለማጥፋትና ሰላም ለማስፈን የተጀመረው ጥረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት አምጥቷል፡፡ ''ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶክተር አቢይ አህመድ የወሰዱት ቁርጠኛ አቋም በወጣቱ አዕምሮ ዘላለም የሚታወስ ነው'' ብሏል፡፡ ከተመረጡ ጀምሮ በህዝቡ ዘንድ ብሄራዊ አንድነትን ለማጠናከር የሚያደርጉት ጥረት ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርም ገልጿል፡፡ ወጣቱ ለነገ ሠላማዊ የሃገር ግንባታ የፊት ተዋናይ በመሆን አሻራውን ማሳረፍ እንዳለበትም መልእክቱን አስተላልፏል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም