በህግ ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ ሲሳተፉ የተገኙ ስምንት ግለሰቦቸ ተያዙ - ኢዜአ አማርኛ
በህግ ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ ሲሳተፉ የተገኙ ስምንት ግለሰቦቸ ተያዙ
ጎንደር፣ መስከረም 23/2013 (ኢዜአ ) አዲሱን የብር ኖት ለውጥ ተከትሎ ያለንግድ ፈቃድ ህገ-ወጥ የቁም እንስሳት ግብይት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ የተገኙ ስምንት ግለሰቦች መያዙን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጠገዴ ወረዳ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
አዲሱ የገንዘብ ለውጥ ከተጀመረ ወዲህ በአካባቢው ከፍተኛ የእንስሳት ግብይት ከወትሮው በተለየ ጨምሮ መታየቱ ተመልክቷል።
የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ጀንበሩ ሙሉ ለኢዜአ እንደተናገሩት ግለሰቦቹ የተያዙት ንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው በዞኑ ከሚገኙ ወረዳዎችና መተማ ጭምር በህገ-ወጥ መንገድ የገዙዋቸውን የቁም እንስሳት በድብቅ ወደ አጎራባች አካባቢ በማጓጓዝ ለመሸጥ ሙከራ ሲያደርጉ ተደርሶባቸው ነው።
ግለሰቦቹ የተያዙት በወረዳው ውስጥ እንደሆነ አመልክተው፤ 355 በሬዎች ፣ 134 በግና ፍየሎችን በህገ-ወጥ መንገድ ግብይት ለመፈጸም ሲያንቀሳቀሱ መገኘታቸውን ገልጸዋል።
በህገ-ወጥ የእንስሳት ግብይት በነባሩ የብር ኖት አንድ በሬ እስከ 60 ሺህ ብር በሚደርስ ግዥና ሽያጭ እየተገበያዩ መሆኑን ፖሊስ መረጃ እንደደረሰው ተናግረዋል፡፡
ፖሊስ በህገ ወጥ ንግዱ ተሰማርተዋል ያላቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ መጀመሩን አመልክተው፤ እንስሳቱንም በኤግዚቢትነት መያዙን አስረድተዋል፡፡
የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አይቸው ታረቀኝ በበኩላቸው አዲሱን የገንዘብ ለውጥ ተከትሎ በአካባቢው ከፍተኛ የእንስሳት ግብይት ከወትሮው በተለየ ጨምሮ መታየቱን ተናግረዋል፡፡
ህገ-ወጥ የእንስሳት ግብይትና ዝውውርን ለመቆጣጠርም የዞኑ አስተዳደር የጸጥታ መዋቅሩን ያካተተ ግብረ ኃይል በማቋቋም ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡
በሌላም በኩል ህጋዊ የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው ከ54 ሺህ ሊትር በላይ ፈሳሽ የምግብ ዘይት ወደ አዲስ አበባ በህገ-ወጥ መንገድ ሲያጓጉዙ የተገኙ አምስት ነጋዴዎችም በህግ ጥላ ስር መዋላቸውም ተመልክቷል፡፡