ማስተባበሪያ ም/ቤቱ በየደረጃው ካሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችና ከዳያስፖራ ማህበረሰቡ ጋር በትብብር እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ማስተባበሪያ ም/ቤቱ በየደረጃው ካሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችና ከዳያስፖራ ማህበረሰቡ ጋር በትብብር እየሰራ ነው
መስከረም 23/2013 (ኢዜአ) የህዝብን ተሳትፎ ለማሳደግ በየደረጃው ካሉ የክልል ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችና ከዳያስፖራ ማህበረሰቡ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ብሔራዊ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽ/ቤት ገለጸ።
ግድቡን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ አጠናክሮ በማስቀጠል ግድቡ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል።
በምክር ቤቱ የህዝብ ግኙነት ሃላፊ አቶ ሃይሉ አብርሃም እንደገለጹት ግድቡን በፍጥነት አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ሲዳማን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ካሉ ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ጋር በትብብር እየተሰራ ነው።
ምክር ቤቱ የተለያየ ይዘት ያላቸው መልዕክቶችን በመቅረጽና ከስራ አስፈጻሚው ጋር በማጽደቅ ወደ ክልሎች አውርዶ የህዝብ ንቅናቄው አብሮ ይሰራል፡፡
በየሩብ፣ በየግማሽና በአመቱ መጨረሻ ከቅርንጫፍ ማስተባበሪያዎች ጋር በመገናኘት እቅድ የጋራ ይደረጋል እንዲሁም ስራን አንድ ላይ በመገምገም ጠንካራ ጎኖች እንዲቀጥሉ የተስተዋሉ ክፍተቶች ደግሞ እንዲታረሙ ይደረጋል ብለዋል አቶ ሃይሉ።
የክልል መዋቅሮች ስራቸውን እንደየ አካባቢያቸው ነባራዊ ሁኔታ የማቀድና የመተግበር አሰራር ያላቸው ቢሆንም በቅንጅት የሚያሰሩ እቅዶችን ይወስዳሉ ብለዋል።
የግድቡን ሁኔታ በተመለከተና ህዝባዊ ተሳትፎው በአጠቃላይ ያለበትን ሁኔታ በየጊዜው በመገናኘት መረጃ የመለዋወጥ ስራ እንደሚሰራም ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በጋራ ከሚሰሩ ስራዎች መካከል ሰልፎችንና ሩጫዎችን ማዘጋጀት ፣የቦንድ ሳምንት ሲኖር በጋራ ማካሄድ የሙዚቃና መሰል የኪነ ጥበብ ምሽት በማዘጋጀት የህዝብ ተሳትፎው እንዳይቀዛቀዝ ይደረጋል ብለዋል አቶ አብርሃም።
ብሄራዊ ም/ቤቱ እና የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በመካከላቸው ያለው ግንኙነት የአዛዥና የታዛዥ ሳይሆን የትብብር መሆኑንም ገልጸው፤ “̎እኛ ለነሱ ትልቅ አቅም ነን፣ እነሱም ለኛ ትልቅ አቅም ናቸው” ብለዋል።
በዚህም በአጠቃላይ የግድቡ ግንባታ ይፋ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በቅንጅት በተሰራው ስራ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 13 ቢሊዮን 790 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል።
በ2013 ዓ/ም በጀት ዓመት ደግሞ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱን በመግለጽ።
በተለይ ይህ አመት የመጀመሪያው የውሃ ሙሊት የተካሄደበት በመሆኑ ከወትሮው ለየት ያደርገዋል ያሉት ሃላፊው ሰፊ የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር የተሻለ ገቢ ሊገኝ እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ብሄራዊ ማስተባበሪያ ም/ቤት ጽ/ቤቱ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ከዲያስፖራ ማህበረሰቡ ጋር ውጤታማ ስራዎችን መሰራቱም ተገልጿል።
ዲያስፖራው ከሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ ባሻገር በሞራልና በፕብሊክ ዲፕሎማሲው ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
በተለይ ዲያስፖራው አዲሱ ሚዲያንና የተለያዩ የህትመትና የብሮድካስት ሚዲያዎችን በመጠቀም አለማቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ላይ የያዘችውን በጋራ የእንልማ አቋም በተለያዩ ቋንቋዎች በማሳወቁ ረገድ የማይተካ ሚና ማበርከቱን ተናግረዋል።
በ2012 ዓ/ም በአለም ሀገራት የሚገኙ 63 ቆንስላዎችን በማስተባበር ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚውል ከ71 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰቡን የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን ግርማ ናቸው።
አቶ ወንድወሰን እንዳሉት የግድቡ የመጀመሪያ ውኃ ሙሌት ከተጠናቀቀ በኋላ ዲያስፖራው በዕውቀትና በገንዘብ ለመደገፍ ከፍተኛ መነሳሳት አሳይቷል።
በቀጣይም ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ዳያስፖራው ስለግድቡ ጥቅም ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ የማስረዳትና የገንዘብ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ኤጀንሲው የማስተባበር ሥራውን በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።