የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ የመድን ሽፋን ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ የመድን ሽፋን ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ መስከረም 22/2013 ( ኢዜአ) በአፍሪካ ግዙፍ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞቹን ደህንነት ታሳቢ ያደረገ የኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ የመድን ሽፋን ይፋ አደረገ።
የመድን ሽፋኑ የጤና መድንን የያዘ ሲሆን መንገደኞች ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ በሚገጥማቸው ችግር ከአገር የማስወጣት፣ ወደ አገር መመለስና ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ ወጪዎችን ለመሸፈን የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
የመድን ሽፋኑ ከመስከረም 21 ቀን 2013 ዓ.ም እስከ መጋቢት 22 ቀን 2013 የሚቆይ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የመድን ሽፋኑ ከአየር መንገዱ ቢሮ ትኬት የቆረጡ ሁሉንም ተጓዦች የሚያጠቃልል መሆኑን አየር መንገዱ ለኢዜአ በላከው መግለጫው አስታውቋል፡፡
አየር መንገዱ የሼባ ምቾትን ያሟላ ተጨማሪ የደህንነት እርምጃ በመውሰድ የደንበኞቹን ደህንነት የሚጠብቅ ሲሆን በተረጋጋ አዕምሮ በረራቸውን እንዲያከናውኑ ጥረቱን እንደሚገፋበት አስታውቋል፡፡
መንገደኞች በጉዞ ላይ ሳሉ የኮቪድ ሕከምና የሚከታተሉ ከሆነ እስከ 100 ሺህ ዩሮ የህክምና ወጪያቸው የሚሸፍንላቸው ሲሆን በተጨማሪ ለ14 ቀናት የለይቶ ማቆያ ክፍያ በየዕለቱ እስከ 150 ዩሮ እንደሚሸፍንም ተገልጿል፡፡
የሼባ ምቾት አገልግሎት ከአገር ማስወጣትንና ወደ አገር መመለስን በተመለከተ ለ7 ቀናት እና 24 ሰዓት ዝግጁ በመሆን አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል፡፡.
የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወልደ ገብረማርያም ሽፋኑን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት "ይህንን ተጨማሪ የደህንነት እርምጃ በመውሰድ ፈር ቀዳጅ ከሆኑት አየር መንገዶች ተርታ በመሰለፋችን ደስተኞች ነን፡፡ በዚህም የደንበኞቻችንን በራስ መተማመን ከፍ ለማድረግ የሚረዳውን ዓለም አቀፉን የኮቪድ-19 መድን ሽፋንን አቅርበናል፡፡" ብለዋል።
የሼባ ምቾት የመድን ሽፋን የመንገደኞችን ጤንነትና ደህንነት ለማረጋገጥ ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል እንደሚካተትም ነው የገለጹት።
"የጉዞ ደህንነት አጠባበቅ በየቀኑ ስለሚለዋወጥ እኛም ለውጡን ተከትለን በፍጥነት አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ግንባር ቀደም ነን፤ የደንበኞቻችንን ደህንነት መጠበቅ ቀዳሚ ተልኳችን ነው" ብለዋል፡፡
የሼባ ምቾት የመድን ሽፋን አገልግሎት ይፋ የተደረገው በኤ.አከስ.ኤ ፓርትነርስና በአዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ሲሆን ሽፋኑ የደርሶ መልስ በረራ ለሚያደርጉ ደምበኞች ለ 92 ቀናት ሲቆይ ለነጠላ ወይም ለአንድ ጊዜ በረራ ደግሞ ለ31 ቀን ይሆናል፡፡