ቀጥታ፡

መሪ የልማት ዕቅዱ ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት ትኩረት መስጠት አለበት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያ በቀጣይ አሥር ዓመታት የምትመራበት መሪ የልማት ዕቅድ ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት ትኩረት መስጠት እንዳለበት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ።

የፕላንና ልማት ኮሚሽን በ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ላይ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪና ተወካዮች ጋር ዛሬ ተወያይቷል።

የልማት ተጠቃሚነትና ማህበራዊ አካታችነትን ማረጋገጥ፣ የኢንቨስትመንትና የሥራ አካባቢን ምቹ ማድረግ፣ ዘላቂ ሰላም ማምጣትና ቀጠናዊ የምጣኔ ሃብት ትብብርን ማረጋገጥ የዕቅዱ የትኩረት መስኮች ናቸው።

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት በአማካኝ10 ነጥብ 2 በመቶ ለማሳደግ መታቀዱን የፕላን ኮሚሽነሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ ዕቅዱን ሲያቀርቡ ገልጸዋል።

ሊቀነስ የሚገባው የድህነት መጠን፣ የተገነቡ ጥቅል አገራዊ አቅሞች፣ በምጣኔ ሃብት ውስጥ ሊፈጠር የሚችለው የኢንቨስትመንት ፍሰት በዕድገቱ በታሳቢነት ተቀምጠዋል።

ኢንዱስትሪ በ13 በመቶ እድገት እንዲኖረው የታቀደ ሲሆን የማምረቻው ዘርፍ 20 ነጥብ 6 በመቶ እድገት ይኖረዋል ተብሏል።

የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ ደግሞ በአማካኝ 8 ነጥብ 2 በመቶ እንደሚያድግ መታቀዱን ነው ኮሚሽነር ፍጹም ያብራሩት።

ኢትዮጵያ 19 በመቶ ህዝቧ ከድህነት ወለል በታች የሚገኝ በመሆኑ እድገት ማምጣት አማራጭ የሌለው መሆኑን በአጽዕኖት ገልጸዋል።

የቀረበው የእድገት ትንበያ ተግባራዊነት፣ ዕቅዱ መነሻ ያደረገባቸው ነጥቦች፣ ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነትና ሌሎች ነጥቦችን አስመልክቶ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች በውይይቱ ላይ አንስተዋል።

መሪ የልማት ዕቅዱ ትኩረት ካደረገባቸው ዋነኛው የዜጎችን ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት እድገት ብታስመዘግብም ዜጎች ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዳልነበሩ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ገልጸዋል።

የመሬት አጠቃቀም፣ ሙስና፣ ሰላምና መረጋጋት፣ ድህነት ቅነሳና ሌሎች ጉዳዮችን የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችና መሪዎች አንስተው ተወያይተውባቸዋል።

የአሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅዱን የጋራ ለማድረግ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የተነሱ ሃሳቦች በዕቅዱ ውስጥ በግብአትነት እንደሚታዩም ኃላፊዎች አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም