በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሰራተኞች ፍልሰትን ለማስቀረት የሚያስችል የመረጃ ማዕከል ተቋቋመ

ሀዋሳ መስከረም 22/2013(ኢዜአ) በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ እያጋጠማ ያለውን የሰራተኞች ፍልሰት ለማስቀረት የሚያስችል የመረጃ ማዕከል ዛሬ ተመረቀ።

በምረቃው ሥነ ሥርዓት የፓርኩ  ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍፁም ከተማ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት  ማዕከሉ የተቋቋመው "ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ  ዩ ኤስ አይዲ ዎርከርስ ዌልነስ አልያንስ ፕሮጀክት "ጋር በመተባበር ነው።

አዲስ ለተቀጠሩ ሠራተኞች ጥቅል መረጃ የሚሰጠው ይህ ማዕከል በመረጃ እጦት በፓርኩ ሲያጋጥም የነበረውን ከፍተኛ የሰራተኞች ፍልሰት ለመከላከል ይረዳል ብለዋል።

ካሁን በፊት በርካታ የፓርኩ ሰራተኞች ስለፓርኩና ሀዋሳ ከተማ ትክክለኛ መረጃ ባለማግኘት ተስፋ ቆርጠው ወደ ቤተሰቦቻቸው የመመለስ እድላቸው ሰፊ መሆኑን አመልክተዋል።

ይህንን ችግር ለመፍታት በፕሮጀክቱ አማካኝነት ጥናት ተካሂዶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማዕከሉ ሊከፈት መቻሉን ተናግረዋል።

የማዕከሉ ዓላማ አዲስ የሚቀጠሩ ሰራተኞች በፓርኩና ከፓርኩ ውጪ አስፈላጊው መረጃ እንዲኖራቸው በማድረግ  ስራቸውን ተረጋግተው እንዲሰሩ ማስቻል ነው ብለዋል።

የማዕከሉ መከፈት ሰራተኞች ሙሉ መረጃ ኖሯቸው እንደፈለጉ  ተንቀሳቅሰው በስራቸው ላይ ውጤታማ ከማድረግ ባሻገር የሰራተኛ ፍልሰትን  በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንሰው ሥራ እሰኪያጁ አብራርተዋል።

የ "ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ዩ ኤስ አይዲ ዎርከርስ ዌልነስ አልያንስ ፕሮጀክት " ተጠባባቂ ማናጀር አቶ ሂካ አለሙ በበኩላቸው ማዕከሉ በፕሮጀክቱ በ3 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እያካሄደ ያለው እንቅስቃሴ አካል መሆኑን ገልጸዋል።

ለአራት ዓመታት በሚቆየው ይሄው ፕሮጀክት ወደ ፓርኩ የሚመጡ ሰራተኞች ሃዋሳ በሚደርሱበት ወቅትና በሂደት ከማህበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ድጋፍ  እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

እንዲሁም ፆታዊ  ጥቃት ለመከላከል፣ እያደገ ከመጣው የህዝብ ቁጥርና እየተስፋፋ ካለው ኢንዱስትሪ የከተማው ማህበረሰብ ሊጠቀም የሚችልበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ማዕከሉን ለመክፈት በፕሮጀክቱ አማካኝነት የፍላጎት ዳሰሳ መነሻ ጥናትና  የማህበረሰብ ውይይትም መካሄዱን አስረድተዋል።

በጥናቱ መሰረት በመረጃ እጥረት ሶስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውሰጥ ከፓርኩ ሰራተኞች 60 በመቶው  ስራ እንደሚለቁ ጠቁመዋል።

በብዛት ከገጠር የሚመጣውን የሰው ኃይል ፍልሰትን ለመከላከል የመረጃ ማዕከሉ መከፈት ወሳኝ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  በፓርኩ የኢንዱስትሪ ሠላም ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ጌታቸው ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሃያ ሁለት ኩባንያዎች የማምረቻ ቬድ ወስደው የተለያየ የአልባሳት ምርቶቻቸውን ለውጭና ሀገር ውስጥ  ገበያ እያቀረቡ እንደሚገኙና 30 ሺህ ለሚጠጉ ሰዎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም